በኬንያ ምርጫ የ23 ዓመት ወጣት ለምክር ቤት አባልነት አሸነፈ

ነሐሴ 05፣2009

ሰሞኑን በተካሄደው የኬንያ አጠቃላይ ምርጫ የተዋዳደረው የ23 ዓመት ወጣት የህዝብ ይሁንታን አግኝቶ  የምክር ቤት አባል ለመሆን መብቃቱ ተነገረ፡፡

የፓርቲ አባል ሳይሆን በግል የተወዳደረው ወጣት ጆን ፖል ምዊሪጊ የሶስተኛ ዓመት የዮኒቨርስቲ ተማሪ ነው፡፡

ወጣቱ የሀገሪቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቀላቀለውም በተወዳደረበት የምርጫ ጣቢያ ተፎካካሪዎቹን በሰፊ ልዮነት ካሸነፈ በኋላ ነው ተብሏል፡፡

ጆን ፖል ‹‹ግምቢ›› በተባለ የምርጫ ጣቢያ ያሉ መራጮችን በምክር ቤቱ ለመወከል ሲወዳደር ምርጫ ቅስቀሳውን ያካሄው እዚህ ግባ ሊባል በማይችል በጀት ነበር፡፡

በዚህም ተቀናቃኞቹ በእረብጣ ብር እና በሚያምር መኪና ምርጫ ቅስቀሳቸውን ቢያደርጉም የወጣቱን ህልም ሊያኮላሹ አልቻሉም ነው የተባለው፡፡  

እናትና አባቱን በሞት የተነጠቀው አዲሱ ተመራጭ ከምርጫው ድል በሃላም ለተወከለበት ምርጫ ጣቢያ ነዋሪዎች በአካባቢው ያለውን ግብርና ለመደገፍና ስራ ፈጠራን ለማበረታታ ማቀዱን ተናግሯል፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 አባቱ ከዚህ አለም በሞት ሲለዮ ተስፋ እንደቆረጠ የተናገረው ፖል አንድ ቀን ተኝቶ በህልሙ በፓርላማ ውስጥ ንግግር ሲያደርግ በማየቱ በሀገሪቱ ፖለቲካ እንዲገባ መነሳሳት እንደፈጠረበት ገልጿል፡፡

በዚህ ሳምንት ማከሰኞ በተካሄደው የኬንያ አጠቃላይ ምርጫ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ በቅድመ ምርጫ ውጤት ተፎካካሪያቸውን ራይላ ኦድንጋ በሰፊ ልዩነት ማሸነፋቸው ተነግሯል፡፡

ሆኖም በይፋ በሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ያልተገለፀውን የምርጫ ውጤት እንደማይቀበሉት የሚናገሩት ራይላ ኦድንጋ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል እየሞገቱ ይገኛሉ፡፡

በአንፃሩ የሀገሪቱን የምርጫ ሂደት የተካታተሉ ታዛቢዎች በምርጫው ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ በአመዛኙ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሀዊ እንደሆነ ምስክርነታቸውን ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፦ሲጂቲኤን ድረ-ገጽ