በአውሮፓ 15 አገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ በኬሚካሎች የተበከሉ እንቁላሎች ሊወገዱ ነው

ነሐሴ 05፣2009

በአውሮፓ በ15 አገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ለጤና ጠንቅ የሆኑ የተበከሉ እንቁላሎች ከገበያ ላይ ተሰብስበው እንዲወገዱ የአውሮፓ ጤና ጥበቃ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

 

በፀረ ተባይ መድሀኒት እንደተበከሉ የሚነገርላቸው እንዚህ እንቁላሎች ስዊዘርላንድና ኦንግ ኮንግን ጭምሮ በ15 የአውሮፓ ሀገሮች እንደተሰራጩ ተነግሯል፡፡

ለሀገሮቹ ገበያ የቀረቡት እንቁላሎች መበካላቸው የታወቀው በኔዘርላንድስ አርሶ አደሮች ይዞታዎች ላይ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ፀረ-ተባይ መድሀኒቶች መገኘታቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

ይሁን እና ለችግሩ መከሰት ማን ነው ተጠያቂ ለሚለው በአውሮፓ ሀገሮች መካከል በተለይም ቤልጄየም፣ ኔዘርላንድና ጀርመን እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ለችግሩ እልባት ለመስጠትም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በጉዳዮ ዙሪያ የሚመለከታቸውን የአባል ሀገራቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት በፊታችን መስከረም ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል፡፡

በጉዳዮ ዙሪያ የአውሮፓ ሀገሮች እራሳቸውን ነፃ ለማውጣት እርስ በርስ ከሚወነጃጀሉ ይልቅ ከችግሩ በመማር በመፍትሄው ዙሪያ በጋራ መስራት እንዳለባቸው የአውሮፓ ህብረት የጤና ኮሚሽነር ቪይቴኒስ አንድሩካቲስ አሳስበዋል፡፡

እንደ ማሳያ በብሪታኒያ ገበያ ከተገመተው በላይ 700 ሺህ የሚጠጋ በፀረ ተባይ መድሃኒት የተበከሉ እንቁላሎች መሰራጨታቸውን ተነግሯል፡፡ 

አብዛኞቹ እነዚህ እንቁላሎችም በአውሮፓ በሚመረቱ እንደ ብስኩት፣ ኬክ በመሰሉ የተቀነባበሩ ምግቦች ውስጥ እንደ ግብዓት ተቀላቅለው እንዳይሆን ተፈርቷል፡፡

እንቁላሎቹ ‹‹ፊፕሮኒል›› በተባለ መርዛማ ፀረ-ተባይ መድሀኒት የተበከሉ ሲሆን መድሀኒቱም በእንስሳቶች የሚገኙ እንደ መዥገር የመሰሉ ነፍሳቶችን ለመግደል ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡

ይህም በመሆኑ መድሀኒቱ የሰብል ጎተራን ማጽዳትን ጨምሮ በማንኛውም የምግብ ሰንሰለት ውስጥ ጥቅም ላይ ለማዋል የተከለከለ ነው፡፡

መድሀኒቱን በማሰራጨት በሰዎች ጤና ላይ አደጋ ፈጥረዋል ተብሎው የተጠረጠሩ የሁለት ኩባንያ ሀላፊዎችም በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተመልክቷል፡፡

ምንጭ፦ስካይ ኒውስና ቢቢሲ