በኡጋንዳ ከፖሊስትሮን ፎም የሚሰሩ ቤቶች የቤት ዋጋ በ30 በመቶ እንዲቀንስ አስችሏል

ነሀሴ9 ፤2009

በኡጋንዳ ከፖሊስትሮን ፎም የሚሰሩ ግድግዳዎችን በሽቦ በማጣመርና በላዩ ላይ ኮንክሪት በማልበስ የመኖሪያ ቤቶችን በአጭር ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ መገንባት መቻሉ ተገለፀ፡፡

በአገሪቱ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የቀረበውን ቴክኖሎጂ እውን ያደረገው ከአውሮፓ የመጣው ዎልፍጋንግ ኤንደርሊን የተሰኘ የህንፃ ግንባታ ባለሞያ ነው፡፡

እንደ ባለሞያው ገለጻ በአዲሱ ቴክሎሎጂ የሚገነባ መኖሪያ ቤት በተለምዶ በብሎኬትና በሲምንቶ ከሚገነባው ቤት በ5 እጥፍ የሚጠነክር ሲሆን የግንባታ ወጪውም 30 በመቶ ይቀንሳል ብሏል፡፡ ቤቱ እሳት የመቋቋም አቅም እንዳለውም ነው የተገለፀው፡፡

በቀድሞ የግንባታ ቴክኖሎጂ በአንድ ፕሮጀክት 1ሺ ግንባታዎችን ማከናወን ቢቻል፣ በአዲሱ ቴክኖሎጂ በአንድ አመት ውስጥ 5ሺ ግንባታዎችን ማከናወን እንደሚቻል  ባለሞያው አብራርቷል፡፡

የቴክኖሎጂው ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆንም ቅሉ ከፎም የተሰራውን የግንባታ ጥሬ እቃ ከውጭ ተገዝቶ የሚገባ በመሆኑ ወጪን ያስወድደዋል ተብሏል፡፡

ኡጋንዳ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቅረፍ በአመት 200 ሺህ ያክል አዳደስ ቤቶች  ያስፈልጓታል፡፡ 

ምንጭ፡- ሲጂቲኤን