የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የ2ዐ1ዐ በጀት 15.5 ቢሊዮን ብር እንዲሆን አፀደቀ

ሐምሌ 08፣2009

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ም/ቤት የክልሉን የ2ዐ1ዐ በጀት 15.5 ቢሊዮን ብር እንዲሆን  አፀደቀ፡፡

ለ2 ተከታታይ ቀናት በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ መደበኛ ጉባኤም ከበጀቱ በተጨማሪ ሌሎች 3 አዋጆችን አፅድቋል፡፡

በጀቱ በ2ዐ1ዐ በጀት አመት ለሚከናወኑ የውሃ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ፣ግብርና፣ መስኖ እና ሌሎች ድህነት ተኮር የልማት ፕሮግራሞች የሚውል ነው፡፡

በጉባኤው ላይ የ2ዐዐ9 በጀት አመት የክልሉ የመንግስት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቧል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀመድ ኡመር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በበጀት አመቱ የተከሰተው ድርቅ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ለህብረተሰቡ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምክር ቤቱ የክልሉን ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2ዐዐ9 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም አዳምጧል፡፡

የክልሉን ንግድ፣ ትራንስፖርትና ኢንዱስትሪ ቢሮ በአዲስ መልክ ለማቋቋም፣ የስራ እድልና የልማት ኤጀንሲና የክልሉን የእንስሳት ግብይት ኤጀንሲን ለማቋቋም የቀረቡ አዋጆችንም አፅድቋል፡፡

ምንጭ ፡‑ የሶማሌ ክልል የመገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ