ከአ.አ 2000 ወዲህ የአለም የረሀብ መጠን መቀነሱን ተገለፀ

ጥቅምት 03፣2010

የአለም የረሀብ መጠን እ.ኤ.አ ከ2000 ወዲህ በ25 በመቶ መቀነሱን ዓመታዊ የአለም ረሀብ ምልከታ መረጃ ገለፀ፡፡

ግጭትና የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ውጤቱን እየቀለበሱት እንደሆኑ ተነግሯል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ከ119 የአለም ሀገራት መካከል ግማሽ ያህሉ እጅግ አስደንጋጭ የረሀብ ችግር እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ መካከለኛው አፍሪካ በችግሩ ክፉኛ በመጠቃት ቀዳሚ ስትሆን ቻድ፣ ሴራሊዮን፣ ማዳካስካርና ዛምቢያ በቅደም ተከተል የረሀብ አደጋው ሰለባ ናቸው ተብሏል፡፡

በበርካታ የአለም ሀገራት ረሀብን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት በረጅም ርቀት የሚያጋጥሙ ተጋዳሮቶች ፈተና እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የከፋ ረሀብ ቀውስ በሚስተዋልባቸው ሀገሮች የሚኖር ግማሽ ያህሉ ህዝብ የምግብ እጥረት እንደሚያጋጥመው ተመልክቷል፡፡

ግጭት፣ የአለም ንብረት ለውጥና ሌሎች ተግዳሮቶች የአለም ረሀብን ለመቀልበስ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እንቅፋት ሆነው ከቀጠሉ እ.ኤ.አ በ2030 የአለም ረሀብን ለማጥፋት የተቀመጠውን የዘላቂ ልማት ግብ ማሳካት እንደማይቻል ተገልጿል፡፡

በቅርቡ የወጣው የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ደግሞ የአለም የረሀብ መጠን ከአስር ዓመት በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መጨመሩን ጠቅሶ 11 በመቶ የሚሆኑው የአለም ህዝብም የችግሩ ተጋላጭ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ሴቶች፣ ህፃናትና አናሳ ህዝቦች የችግሩ ዋና ተጠቂዎች ሲሆኑ ከዚህም ውስጥ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በችግሩ ህይወታቸው ከሚያልፉ ሰዎች ግማሽ ያህሉን ይሸፍናሉ ተብሏል፡፡

ምንጭ፦ ሲጂቲኤን ድረ-ገጽ