ኢትዮጵያ በ2016 ብቻ ለታዳሽ ኃይል 100 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ አድርጋለች፥ ሪፖርት

ጥር 17፣2009

ኢትዮጵያ ባለፈው የአውሮፓዊያኑ አመት 100 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ በማድረግ በታዳሽ ኃይል ልማቱ ዘርፍ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ተርታ መሰለፏን አለም አቀፉ  የታዳሽ ኃይል ኤጄንሲ አስታወቀ።

አለም አቀፉ  የታዳሽ ኃይል ኤጄንሲ "ዘ  ሪኔዌቤል ግሎባል ስታተስ" በ2016 ሪፖርቱ  እንዳመለከተው ኢትዮጵያ  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ   ከፀሀይ  ኃይል የሚያመነጩ  መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ አውላለች። በእያንዳንዱ የገጠር አርሶ  አደር ቤት ደግሞ በቦዮ ቴክኖሎጂ የሚሰሩ ከአራት ሚሊዮን በላይ የምግብ  ማብሰያ  ምድጃዎች ጥቅም ላይ እንዲዉሉ  በማድረግ  ከግንባር ቀደም የአፍሪካ  አገራት ጋር በመሰለፍ የ5ኛ   ደረጃን ይዛለች ብሏል።

ደቡብ አፍሪካ  ቀዳሚውን ደረጃ  ስትይዝ ሞሮኮ በሁለት ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛ፣ኬንያ በ357  ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ እንዲሁም ዩጋንዳ በ134 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ታዳሽ የኃይል ዘርፍ  አማራጮችን ጥቅም ላይ በማዋል አራትኛ ደረጃን ይዛለች።

ኢትዮጵያም በፀሐይና  በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጭ አድርጋ በመስራቷ አመታዊ ሪፖርቱ  በአምስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።  

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ  እ አ አ ከ 2015  ወዲህ የአፍሪካ  አገራት ለታዳሽ ኃይል ልማት የሰጡት ትኩርት እያደገ  በመምጣቱ የታዳሽ ኃይል አመንጪና የባዮ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በብዛት ጥቅም ላይ እየዋሉ  ነው።