ከሰሃራ በታች የሚገኙ የሞባይል ተጠቃሚዎች በ2020 ከ500 ሚሊዮን ሊበልጥ ይችላል

ሐምሌ 04፤2009

ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር እ.ኤ.አ በ2020 ከ500 ሚሊዮን ሊበልጥ እንደሚችል ዓለማቀፍ የሞባይል አገልግሎት ሰጪዎች ማህበር አስታውቋል፡፡

በአለም ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ ላይ የሚገኘው ቀጠናው እስከ 2016 መጨረሻ 420 የነበረው የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር በ2020 535 ይደርሳል ተብሏል፡፡

የሞባይል ተጠቃሚው ቁጥር መጨመር ለቀጠናው ዓመታዊ ጥቅል ምርት መጨመር፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ለማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም የማህበሩ 2017 ሪፖርት  ያመለክታል፡፡

አዲስ ከሚመጡት የሞባይል ተጠቃሚዎች 115 ሚሊዮን የሚሆኑት ከኢትዮጵያ፣ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከናይጄሪያና ከታንዛኒያ እንደሚሆኑም ነው በሪፖርቱ የተገለጸው፡፡

ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት የሞባይል ኢንዱስትሪው 110 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፤ ከ270 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሞባይላቸው የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ሲሆኑ የሞባይል የገንዘብ ዝውውር ላይ የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ 280 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

ምንጭ፡ ሺንዋ