ድብርት 300 ሚሊዮን የአለማችን ሰዎችን ተጎጂ ማድረጉን የአለም ጤና ድርጅት ገለጸ

የካቲት 17፣ 2009

ድብርት 300 ሚሊዮን የአለማችን ሰዎችን ተጎጂ ማድረጉን የአለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

ዘውታሪ የመንፈስ ጭንቀት ወይም ድብርት ፣በአዘቦት ደስታ  የሚፈጥሩ  ስራዎች ሳይቅሩ ስሜት ማጣትና ዕለታዊ ክንዋኔዎችን  መፈፀም አለመቻልና ለሀዘን በማጋለጥ ብዙዎችን ለጉዳት መዳረጉን ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርቱ አመልክቷል።  

በመንፈስ ጭንቀት ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች፣ ወጣቶችና አዛውንቶች መሆናቸው ድርጅቱ ገልጿል፡፡

እንደሪፖርቱ  ከሆነ ከአጠቃላይ የአለም ህዝብ 4 ነጥብ 4 በመቶ ያህሉ በድብርት ተጠቅቷል። ይህ ስሌት  እ ኤ አ ከ2005 - 2015 ባሉት ዓመታት የ18  በመቶ ጭማሬ ማሳየቱ የችግሩ አሳሳቢነት እያደገ መምጣቱን አመላከች መሆኑ  ተጠቁሟል።  

እንደ ሪፖርቱ ዘገባ በየአመቱ በአመዛኙ  ዕድሜያቸው ከ15 እን 29 መካካል የሚገኝ 800 ሺህ ሰዎች ከመንፈስ ጭንቀት ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡በተለይም ዕድሚያቸው ከ60 ዓመት በላይ በሆኑት ችግሩ እየባሰ መምጣቱም ተመልክቷል።  

በመንፈስ ጭንቀት ወይም ድብርት የሚመጣውን ችግር ለመቋቋም የመንግስታቱ ድርጅት በስርዓተ ትምህርት የሚካተት ትምህርት ማዘጋጀትና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በመፍትሄነት አስቀምጧል።

የተለያዩ አካላዊና የስነ ልቦናዊ ህክምናዎች አማራጭ ከድብርት መላቀቂያ መንገዶች መሆናቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል።

ምንጭ፥ ዩ ኤን ዜና  ማዕከል