አለም ባንክ ለ5 የአፍሪካ አገራትና ለየመን ድርቅ 1.6 ቢሊን ዶላር መድቦ እየሰራ መሆኑን ገለፀ

መጋቢት 01 ፣ 2009

የአለም ባንክ በድርቅና ረሃብ ለተጠቁ አገራት አስቸኳይ የዕለት እርዳታ እንዲደርሳቸው የ1.6 ቢሊዮን ዶላር  መድቦ እየሰራ መሆኑን  አስታወቀ፡፡ 

የአለም ባንክ ቡድን በድረ ገፁ ይፋ  ባደረገው መረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ርሃብ ላጠላባቸው እና በአየር መዛባት ምክንያት በድርቅ ለተጎዶ  6 አገራት የሚሆን እርዳታ በአስቸኳይ እንዲደርስ እየሰራ መሆኑን አመልከቷል፡፡

የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት  ጂም  ዮንግ  ኪም እንዳሉት ባንኩ  ችግሩ በተከሰተባቸው አገራት ተጎጂዎች  ምግብና ውሃ እንዲደርሳቸው  ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆቱንና  የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ለማድረግ አሁንም ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአለም ባንክ እስካሁን  ለአገራቱ ከመደበው 1.6 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ በጀት 870 ሚሊን  ዶላር ያህሉ ለተረጂዎች በመድረስ ላይ  መሆኑንም  አመልክተዋል፡፡

ባንኩ ተጨማሪውን  የ770 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በፍጥነት እንዲለቀቅ ግፊት እያሳደሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን አሁን ከመቋቋም በዘለለ  በዘላቂነት እንዳይከሰት ለማድረግ የሚያስችል አቅም በየአካባቢው ለመፍጠር ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የአለም ባንክ ድርቅና የእርስ በርስ ግጭት የተከሰተበቸው  አገራት ብሎ  እርዳታው በአስቸኳይ ለማድረስ ይፋ ያደረጋቸው አገራት አምስት የአፍሪካና አንድ የኢሲያ አገራት ናቸው፡፡

ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ ፣ናይጀሪያ፣ ሶማሊያ ፣ኢትዮጵያና የመን ትኩረት ያገኙ አገራት መሆናቸውን ባንኩ በመገለጫው አመልክቷል፡፡