የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራት ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖችን ሊገዛ ነው

ህዳር 05፤2010

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ አራት ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት ትዕዛዝ ማስተላለፉ ተነግሯል፡፡

በግዢ ስምምነቱ ውስጥም በፓሪስ የአየር ትርኢት ላይ ሁለት አውሮፕላኖችን ለመግዛት የተደረሰውን ስምምነት የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዱባይ የአየር ትርኢት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የግዢ ስምምነቱ አየር መንገዱ የሚሰጠውን የጭነት አውሮፕላን አገልግሎት ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

አውሮፕላኖቹም በሁለት አመታት ውስጥ ተሰርተው ለአየር መንገዱ እንደሚተላለፉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት በስድስት ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይም አየር መንገዱ እስከ 20 የሚደርሱ መካከለኛ መጠን ያላቸውን አውሮፕላኖችን ለመግዛት ፍላጎት ማሳየቱን ሮይተርስ ገልጿል፡፡

እነዚህ አውሮፕላኖች ከ220 እስከ 270 መቀመጫ ያላቸው ሲሆን ለአገልግሎት የሚበቁትም በፈረንጆቹ 2025 ውስጥ ነው ተብሏል፡፡

ምንጭ፡ ፍላይት ግሎባል/ሮይተርስ