14ኛውን የአለም ደም ለጋሾች ቀን በኢትዮጵያ እየተከበረ ነው

ሰኔ7፤2009

ኢትዮጵያ 14ኛውን የአለም ደም ለጋሾች ቀን "ምን ማድረግ ይፈልጋሉ? ደም መለገስ? አሁኑኑ ይለግሱ፣ ሁሌ ይለግሱ፣ መደበኛ ደም ለጋሽ ይሁኑ!!" በሚል መሪ ቃል ከሰኔ 7/2009 ዓ.ም ጀምሮ ማክበር ጀምራለች፡፡

ቀኑ ለተከታታይ 3 ወራት እስከ ጷጉሜ 5/ 2009 ዓ.ም በተለያዩ ፕሮግራሞች መከበሩ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃብተማርያም ደሞዝ ገልፀዋል፡፡

ድንገተኛ አደጋዎችን መቀነስ እና በድንገተኛ አደጋ የተጎዱ ታካሚዎች ከመሞታቸው በፊት እናድን የሚሉ አላማዎች አንግቦ እንደሚከበርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት በአመት ውስጥ ሶስት ጊዜና ከዛ በላይ ደም የሚለግሱ መደበኛ ደም ለጋሾችን ቁጥር ለማብዛት በእንቅስቃሴ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የደም ፍላጎት ለማሟላት ከ250 ሺህ በላይ ቋሚ የደም ለጋሾች ቢያስፈልጉም በአሁኑ ወቅት ግን 10 ሺህ መደበኛ ደም ለጋሾች ብቻ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ 

ዘንድሮ በ9 ወራት በመላው አገሪቱ ከሚገኙ በጎ ፈቃደኛ የደም ለጋሾች ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው 200 ሺህ ዩኒት ደም ውስጥ 134 ሺህ የሚሆነው መሰብሰቡና የእቅዱ 88 በመቶ መፈፀሙን ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 

በአለማችን በተለይም ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ደም የመለገስ ባህል ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ የደም አቅርቦትና ፍላጎት አይጣጣምም፡፡

የደም ልገሳ ባህልን ለማዳበር በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን በማስታወቂያና በተለያዩ ፕሮግራሞች የደም ልገሳ ባህልን ለማሳደግ የኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት እየሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በከተሞች አካባቢ ብቻ በስፋት የሚታየውን የደም ልገሳ ባህልን ወደ ገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎችም ለማስፋፋት በእቅድ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሪክተሩ የጠቆሙት፡፡

በኢትዮጵያ በበጎ ፍቃደኞች የሚለገሰው ደም በነፃ ነው፤ የተለገሰው ደምም ለታካሚ የሚደርሰው በነፃ ነው፤ ደም አይሸጥም ደም አይለወጥም፡፡

ማንኛውም እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነና የሰውነት ክብደቱ ከ45 ኪሎ ግራም የበለጠ ሰው በአገሪቱ በሚገኙ የደም ባንኮች ደም እንዲለግስ የኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ