150 ስደተኞች ሆን ተብለው ወደ ባህር መጣላቸውን ተመድ አወገዘ

ነሐሴ 05፣2009

በየመን ጠረፍ ከ150 በላይ ስደተኞች በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሆን ተብሎ ወደ ባህር መጣላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ አስታውቋል፡፡

በ24 ሰዓት ልዩነት ወደ ባህር ከተጣሉት 150 ስደተኞች 13ቱ የደረሱበት አልታወቀም ብሏል ድርጅቱ፡፡ 6 ስደተኞች ደግሞ ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡

እንደ ተ.መ.ድ የስደተኞች ድርጅት ከሆነ ወደ ባህር ከተጣሉት ስድተኞች  ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል፡፡

ድርጅቱ ከአደጋው ለተረፉ 57 ስደተኞች ምግብ እና ውሃ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል፡፡

ለአደጋ የተጋለጡት ስደተኞች  የመን የደረሱት በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ በሚገኙ ህገ ወጥ  አዘዋዋሪዎች መሆኑን ዘገባው ያትታል፡፡

የተባበሩት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ  ድርጊቱን ክፉኛ አውግዞታል፡፡

ከባለፈው ጥር ጀምሮ 55 ሺህ ስደተኞች ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን መፍለሳቸውን አልጀዚራ ድርጅቱን ወቢ በማድረግ  ዘግቧል፡፡