27 ኤርትራዊያን ስደተኞችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

ግንቦት 2፣2009

ሲሚንቶ የጫነ በማስመሰል 27 ኤርትራዊያን ስደተኞች  አሳፍሮ በሕገ_ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ሲጓዝ የነበረ የጭነት ተሽከርካሪ በጎንደር ከተማ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ከማይፀብሪ የኤርትራ ስደተኞች ካምፕ የተነሳው ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ እቃ መጫኛው ላይ ኮንቴይነር በመጫን እና ከላይ በላሜራ በመበየድ ከዚያም በላዩ ላይ ሲሚንቶ ይጭናል።

ሙሉ በሙሉ ሲሚንቶ የጫነ በማስመሰልም በውስጡ 27 ኤርትራዊያን ስደተኞችን በመያዝ ወደ ሱዳን ለማሻገር ጎንደር ከተማ ይደርሳል።

በከተማው የልደታ ክፍለ ከተማ በውስጥ ለውስጥ መንገድ ሲጓዙ ከላይ የተጫነው ሲሚንቶ ተደርምሶም በሁለት ግለሰቦች ላይ ጉዳት በማድረሱ ህገ ወጥ ስደተኞቹ ባሰሙት የድረሱልን ጩኸት የአካባቢው ነዋሪዎች መኪናውን አስቁመው ለፀጥታ አካላት ይጠቁማሉ።

በዚህም አሽከርካሪው እና ስደተኞቹ በቁጥጥር ስር ውለው በከተማዋ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ምክትል ኮማንደር አያና ሹምየ ተናግረዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ወደ ሆስፒታል መላካቸውንም ምክትል ኮማንደር አያና ተናግረዋል።

ምክትል ኮማንደሩ ህብረተሰቡ ባደረሰው ጥቆማ ስደተኞቹን ከተጨማሪ አደጋ መታደግ በመቻሉ የአካባቢውን ነዋሪ ላደረገው ትብብር ማመስገናቸውን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል።