41 ድርጅቶች የምርቶቻቸውን ዋጋ ማሸሻላቸውን ለባለስልጣኑ አሳወቁ

ህዳር 08፣2010

የብር ዋጋ ተመን ማሸሻያን ተከትሎ 41 የመድሃኒት እና የብረታብረት አምራች እና አስመጪ ድርጅቶች ያደረጉትን የዋጋ ጭማሪ ማሸሻላቸውን የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ድርጅቶቹ መቀነሳቸውን ያሳወቁት ለባለስልጣኑ ነው፡፡

ዋጋ ጭማሪው ላይ የተሳተፉ 45 የመድሃኒት አምራች እና አስመጪ ድርጅቶች ቢሆኑም ዋጋውን ለመቀነስ የወሰኑት 25ቱ ብቻ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

በሀገር ውስጥ ብርታብረት የሚያመርቱ 16 ድርጅቶች ደግሞ ዋጋ መቀነሳቸውን ለባለስልጣኑ አሳውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርቶቹን ተቀብለው የሚቸረችሩ ነጋዴዎች ዋጋውን እንዳልቀነሱ በመግልፃቸው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

በመሆኑም በቀሪዎቹ ድርጅቶች ላይ ባለስልጣኑ ክስ ለመመስረት እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

በብረታብረት ዘርፍ በተሰማሩ አስመጪዎች ላይም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች በአምራቾች የተስተካከሉ ምርቶች በቸርቻሪዎች ዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸው ተገኝቷል ተብሏል፡፡

ባለስልጣኑ ፍተሻ ካደረገባቸው 50 የመዲናዋ ሱፐር ማርኬቶች እና ሀይፐር ማርኬቶች መካከል 25ቱ በስኳር እና መሰል ምርቶች ላይ ጭማሪ ማድረጋቸውን ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡ በመሆኑም በህጉ የተቀመጠው ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡

በገበያ ላይ የሚታየው የግብርና ምርቶች ዋጋ አምና በዚህ ወቅት ከነበረው ዋጋ ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ በባለስልጣኑ ተገልጿል፡፡

በአዝመራው ሞሴ