የአፍሪካ ሕብረት ለአጼ ሀይለስላሴና ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እውቅና ሰጠ

ሰኔ 27፣2009

29ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት ባበረከተችው አስተዋጽኦ የጎላ ሚና ላላቸው የቀድሞ መሪዎች ቀዳማዊ አጼ ሀይለስላሴና  ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ  እውቅና ሰጠ።

29ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ከማላቀቅ አንስቶ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወደ አፍሪካ ሕበረት ላደረገው ሽግግር እንዲሁም ሕብረቱ በአለም መድረክ በአንድ  ድምጽ እንዲቆም መሰረት የጣለችው ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናውንም የወሰዱት ቀዳማዊ ሀይለስላሴና ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ  አፍሪካና አፍሪካውያን ቋሚ ክብር ሊለግሷቸው ይገባል ብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ጠያቂነት የአፍሪካ መሪዎች ለሁለቱ ኢትዮጵያውያን መሪዎች ትልቅ ስፍራ እንዲሰጣቸው መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ቀዳማዊ ሀይለስላሴና ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለአፍሪካና ለህብረቱ ያደረጉትን አስተዋጽኦ የሚዘከርና ውላታቸውን የሚያስታውስ ቋሚ መታሰቢያ እንዲኖራቸው የኢትዮጵያ መንግስት  ተደጋጋሚ የዲፕሎማሲ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታውሰዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ማሻሻያ ላይ በተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ ንቁ ተሳታፊ  ነበረች ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የህብረቱ መሪዎች አብይ አመታዊ ጉባኤያቸው አንድ ጊዜ  በአዲስ አበባ እንዲካሄድና የአከባቢያዊ  ማሕበራት ሚና እንዲጠናከር ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል።

አፍሪካ በሰላምና በጸጥታ ያጋጠሟትን ችግሮች ለመፍታት የምትሰራውን ስራ  በማጠናከር የህብረቱን የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግም መሪዎች ከመከሩባቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ሕብረቱ በኤርትራና በጅቡቲ  ድንበር መካከል ያለውን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ  አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ  29ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በተለይም የሕብረቱን አሰራሮች በማዘመን እና ውጤታማ  በማድረግ ላይ በስፋት መምከሩን ተናግረዋል።

ሪፖርተር:-ፍትህአወቅ የወንድወሰን