የዲያጎ ኮስታ ሰሞነኛ ድርጊት እና ቀደምት ‘ተንኮሎቹ’

ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የቸልሲ እና አርስናል የፕሪሚየር ሊግ  ጨዋታ የቸልሲው ዲያጎ ኮስታ ያሳየው አወዛጋቢ ባህሪ ሰሞነኛ  መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

በዚህ ጨዋታ ኮስታ ለአርስናሉ ተከላካይ ጋብሬል በቀይ ካርድ መውጣት  ምክንያት ነው፡፡ ኮስታ በሌላው የአርስናል ተከላካይ ኮሽሊኒ ላይ ትንኮሳ አድርጓል፡፡

የዲያጎ ኮስታ የነገር ፍለጋ እና የጋብሬል የንዴት እርግጫ ያስከተለው ቀይ ካርድ አሁን በፕሪሚየር ሊጉ አስተዳዳሪዎች እየተመረመረ ይገኛል፡፡

የምርመራው  ውጤት ጋብሬልን ከቅጣት እንደሚያድን ሲጠበቅ ኮስታን ደግሞ ወደ  ቅጣት  እንደሚወስደው ተገምቷል፡፡

ነገር ግን ይህ ድርጊቱ የመጀመሪያው አለመሆኑን ደይሊ ሜል ተከታይ ማስረጃዎች በማቅረብ ያስረዳል፡፡

ኮስታ ከጋብሬል ጋር 2013 /አትሌቲኮ ማድሪድ ቪላሪያል/

የአሁኑ የአርስናል ተከላካይ ጋብሬል ቀድሞ በሚጫወትበት ቪላሪያልም የዲያጎ ኮስታ ጉሽሚያ ደርሶታል፡፡ የዚያን ጊዜው የአትሌቲኮ ማድሪድ አጥቂ ዲያጎ ኮስታ በጨዋታው ጋብሬልን በክርኑ ልቡ አካባቢ ይመታዋል፡፡

በዚህ የተናደደው ጋብሬል ኮስታን በቀይ ካርድ ለማስወጣት በማሰብ ይወድቃል፡፡ ተሳክቶለትም ዳኛው በኮስታ ላይ ቀይ ካርድ መዘዋል፡፡ በዚህም ኮስታ በጋብሬል አሸናፊነት ከሜዳ ወጥቷል፡፡

ከሁለት ዓመታት በኋላ በቸልሲ እና አርሰናል ዳግም ተገናኙ

ሁለቱ ተጨዋቾች ከሁለት ዓመታት በኋላ ዳግም በሌላ ሀገር በሌላ ክለብ ባለፈው ቅዳሜ ተገናኙ፡፡ የዚያኔው ተሸናፊ ዲያጎ ኮስታ ከቸልሲ ጋር በተራው የአርሰናሉን ጋብሬል  አሸነፈ፡፡ በጨዋታው ኮስታ ራሱን ከዳኛው በመደበቅ የፈጠረው የነገር ጉትጎታ ተሳክቶለት ጋብሬልን የቀይ ካርድ ሰለባ አደረገው፡፡ በዚህም  አርስናልም ጋብሬልም እንዲሸነፉ ምክንያት ሆነ፡፡

ኮስታ ከራሙስ ጋር የፈጠረው አለመግባባት /ማድሪድ ደርቢ2012/

በበርናባው የማድሪድ ደርቢ እየተካሄደ ነው፡፡ የሪያል ማድሪዱ ስርጅኦ ራሞስ እና የዚያን ጊዜው የአትሌቲኮው ማድሪዱ አጥቂ ዲያጎ ኮስታ  ተፋጠዋል፡፡ በጨዋታው ኮስታ በእጆቹ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በራሞስ ሲያደርስ ታየ፡፡ የራሞሰን ጭንቅላትም  በእጁ  ወረወረ፡፡ በዚህም ትልቅ ሰጣ ገባ ተፈጠረ፡፡

ኮስታ ከዛብሌታ /ሲቲ ከ ቸልሲ 2014/

ባለፈው ዓመት ነው ቸልሲዎች በፕሪሚየር ሊጉ ሲቲን ለመግጠም ወደ ኢትሃድ አቅንተዋል፡፡ በጨዋታው የማንችስተር ሲቲው የቀኝ ተመላላሽ ፓብሎ ዛብሌታ  በዲያኮ ኮስታ ላይ ጥፋት ይሰራል፡፡ ዳኛውም ቅጣት ምት ይሰጣሉ፡፡ ዛብሌታ ሁለተኛ ቢጫ ካርዱ ስለነበር ከሜዳ መሰናበቱ ግድ ነው፡፡ ዲያጎ ኮስታ ግን በዚህ አልረካም እናም ሂዶ ጉሮሮውን በሁለት እጆቹ አነቀው፡፡ በአጠገቡ የሚገኙት ፈርናንዲኒሆ እና ያያ ቱሬም   የኮስታን እጆች ከዛብሌታ አንገት አላቀዋቸዋል፡፡

ኮስታ ከእነዚህ ተጨዋቾች ጋር ብቻ አይደለም ለጠብ የተዳረገው፡፡ ከሊቨርፑሎቹ ሄንደርሰን እና ኢመር ቻን ጋር ለገላጋይ የሚያስቸግር ትንቅንቅም  አድርጓል፡፡ ጆን ቴሪ እና ዮዋን ካፓይም የኮስታ ተንኮል ደርሷቸዋል፡፡ እናም ዲያጎ ኮስታ ማለት ይህ ነው፡፡

 

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች