አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ አትሌቲክሱን እንደሚያገለግል ገለጸ

ጥቅምት 27፣2009

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ሆኖ የተመረጠው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ አትሌቲክሱን እንደሚያገለግል ገለጸ።

ለአትሌቲክሱ ውጤት ማጣት አንዱ ምክንያት አትሌቶች ልምምዳቸውን በአዲስ አበባ ብቻ ማድረጋቸው በመሆኑ ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ልምምድ የሚሰራ አትሌት አይኖርም ብሏል።

አትሌት ኃይሌ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጋቸው 400 የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ውድድሮች 80 በመቶ ያህሉን በበላይነት ማጠናቀቅ ችሏል።

በኦሊምፒክ መድረክ የሁለት ወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ኃሌ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ደግሞ 27 ክብረ ወሰኖችን መስበር የቻለ ጠንካራ አትሌት ነው።

ኃይሌ ባለፈው ዓመት ራሱን ከአትሌቲክስ ውድድር ያገለለ ሲሆን አሁን ደግሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በመሆን ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በፕሬዚዳንትነት ዘመኑ በአትሌቲክሱ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ እንደሚሰራ ነው አትሌት ኃይሌ ቃል የገባው።

"አትሌቲክስ ደሜ ውስጥ ያለ ነገር ነው፤ ምናልባት ሙሉ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ ጠዋት ተነስቼ የምሰራው እሱን ስለሆነ ቀኑን ሙሉ የምሰራው እሱን ነው፤ በትርፍ ጊዜ የሚሰራ ሥራ አይደለም" ሲል ለሥራው የተለየ ትኩረት መስጠቱን ገልጿል።

"ስፖርት በትርፍ ሰዓት የሚሰራ ሥራ ነው እየተባለ አትሌቲክሳችን ወደ ኋላ ከጎተተብን ነገር አንዱ ነው" በማለት ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጧል።

ለአትሌቲክሱ ውጤት መጥፋት አንዱ ምክንያት እየሆነ ያለው አትሌቶች በአዲስ አበባ ብቻ ልምምድ መሰራታቸውና መኖራቸው እንደሆነም ተናግሯል።

"አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ አትሌቶች አዲስ አበባ ላይ ልምምድ ይሰራሉ ማለት ለኔ ከባድ ነው፤ ምክንያቱ አንዱ ያገኘነው ጥናት አዲስ አበባ ውስጥ እየኖረ ምርጥ ስፖርተኛ መሆንና ምርጥ ስፖርተኛ ማፍራት እንደማይቻል ነው" ሲል ገልጿል።

ስለሆነም አትሌቶች ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው ልምምዳቸውን የሚሰሩበት ኑሯቸው ጭምር ከአዲስ አበባ ውጭ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚመቻች ይደረጋል ነው ያለው።

"አትሌት ኃይሌ መሮጥ እንጂ መምራት አይችልም፤ ለሠራተኛም አይመችም፣ የታላቁ ሩጫ መስራችና ባለቤት መሆኑስ የጥቅም ግጭት አያስነሳም ወይ" ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ በሰፊው መልሷል።

"2 ሺህ እና ከዛ በላይ ሰራተኞች በማስተዳደርበት ድርጅት ውስጥ መምራት አይችልም ከተባለ ድርጅቱ ማን መርቶት ነው እዚህ ያደረሰው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

"ለሰራተኛ በጣም እመቻለሁ ነገር ግን ለሚያሾፍና ለማይሰራ ሰው አልመችም፤ አትሌት በነበርኩበት ጊዜም በቡድን ስራ አምናለሁ አሁንም የቡድን ሥራ ለመስራት ነው የምጥረው" ብሏል።

"የታላቁ ሩጫ መስራችና ባለቤት በመሆኔ ምንም ዓይነት የጥቅም ግጭት አያመጣም፤ የታላቁ ሩጫ ሥራ አሥኪያጁ ሌላ ነው እኔ እንደ ፕሬዝዳንትነቴ ቅድሚያ የምሰጠው ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው።"

አትሌት ኃይሌ ፕሬዝዳንት ሆኖ በመመረጡ ሕዝቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚጠብቅ ከሆነ በሥራ ዘመኑ መጀመሪያ ከሚገጥሙት ፈተናዎች እንዱ እንደሆነ ነው የተናገረው።

"ለዚህ ቦታ የተወዳደርኩት ለውጥ ለማምጣት ነው፤ ለውጥ እንደማመጣ እርግጠኛ ነኝ ነገር ግን ጊዜ ያስፈልጋል" ሲል ተደምጧል።

የፌዴሬሽኑ ዋና ዓላማ ውጤት ማምጣት ነው፤ ውጤት ለማምጣት ደግሞ በአሰለጣጠን፣ በአትሌቶች አመራረጥ፣ ቦታ በመምረጥና ሌሎች ውጤት ሊያስገኙ በሚችሉ ጉዳዮች በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያለው።

በተለይም ተተኪዎች የማፍራት ሥራ ትልቁ ትኩረት የሚሰጠው እንደሆነም አስምሮበታል።

ኮሎኔል ጌታሁን ተክለማርያም፣ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው፣ አቶ ሙሉጌታ ኃይለማርያም፣ ወይዘሮ ብሥራት ጋሻውጠና እና አቶ አለባቸው ንጉሴ እንደቀደም ተከተላቸው ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመው ከ 1941 ዓ.ም ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት መምራታቸውን ኢዜአ  ዘግቧል።

ለቀጣየችው አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመራው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በስፖርቱ ያለፈ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ያደርገዋል።

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች