የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የሁለት ቀናት ወግ አንኳሮች

ህዳር 01፣2010

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንታዊ እና የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ከ45 ቀናት በኋላ እንዲካሄድ አባላቱ ጥቅምት 30፣ በአዲስ አበባ ባካሄዱት መደበኛ ጠቅላላ  ጉባኤያቸው ወስነዋል፡፡

በተለይም ፌደሬሽኑን ላለፉት አራት ዓመታት ሲመሩ የነበሩትን የስራ አስፈፃሚ አባላትና ፕሬዝዳንቱን በአዲስ ለመተካት ጉባኤው ለዛሬ ይዞት የነበረውን አስመራጭ ኮሚቴዎችን ሳይመርጥ መበተኑ ከወዲሁ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

የአስመራጭ ኮሚቴው ምርጫ ለምን አልተካሄድም ተብለው የተጠየቁት የወቅቱ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁኔዲን፣  አባላቱ ስብሰባው ከመጠናቀቁ በፊት መውጣት በመጀመራቸው ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ፊፋ የሚሰጠንን ውሳኔ እናያለንም ብለዋል፡፡  

በመሆኑም በቀጣዩ ምርጫ ዙሪያ የፊፋ መልስ ይጠበቃል፡፡

በመጀመሪያው ቀን ውሎ ምርጫው 68ለ62 በሆነ ድምፅ መራዘሙ ይታወሳል፡፡

ኦሮሚያ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ምርጫው ይራዘም የሚለውን ጎራ ይዘው ታይተዋል፡፡ ደቡብ፣ አዲስ አበባ እና ትግራይ ክልሎች ደግሞ ምርጫው መራዘም የለበትም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

በመድርኩ የታየው አለመደማመጥ እና የቡድን መንፈስ የጉባኤውን መንፈስ ረብሾት ታይቷል፡፡  ይህንን ተከትሎ በእግር ኳሱ አመራሮች ያልታየው ጥሩ ስነ ምግባር እንዴት በተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ሊኖር ይችላል የሚል ጥያቄ ከአባላቱ አስነስቷል፡፡

በዛሬው ጉባኤ ትላንት ከተገኘው ተሳታፊ ቁጥር ከ20 በላይ ያነሰ አባላት እንደተገኙበት የፌደሬሽኑ መሪዎች ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጉባኤው ክፍፍል መፍጠሩ ግልፅ ሆኗል፡፡

እንዲፀድቅ ተሻሽሎ የቀረበው የፌደሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ በጉባኤው እንዳይፀድቅ ተከልክሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ደንቡን ለማየት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡

የ2010 ዓ/ም የፌደሬሽኑ ዕቅድ በደንብ የተገመገመ ባይሆንም ጊዜ ተሻማብን በሚል ምክንያት በጭብጨባ እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡

ምርጫው በመራዘሙ አፋር ክልል አጥቶት የነበረውን ጉባኤውን  የማስተናገድ ዕድል ዳግም አግኝቷል፡፡

በአዝመራው ሞሴ

 

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች