በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው ብሄራዊ ስታዲየም ግንባታ 25 በመቶ ደረሰ

ህዳር 6፣ 2009  

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ እየተገነባ ያለው ብሄራዊ ስታዲየም ግንባታ ስራ 25 በመቶ ደረሰ።

የግንባታ ስራው ከተጀመረ 10 ወራት የተቆጠረ ሲሆን እስካሁን የአፈር ቁፋሮው በመገባደዱ የኮንክሪት ሙሊትና የብረት ማንጠፍ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

የግንባታው ተቆጣጠሪ ኢንጅነር መለሰ ለማ የግንባታ ስራው በተያዘለት ጊዜ ተቃራረቢ  በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ያለው የግንባታ ስራ 25 በመቶ የደረሰ ቢሆንም ከተጀመረበት ቀን አንጻር ግን ግንባታው 30 በመቶ መድረስ ነበረበት ነው ያሉት።

ይህም ሊሆን የቻለው ግንባታው እንደተጀመረ አካባቢ የግንባታ ዕቃዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ ባለመግባታቸው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ኢንጅነሩ ገለፃ  አሁን የግንባታ እቃዎች ሙሉ ሙሉ በመሟላታቸው ስራው በፍጥነት መከናወኑን ይቀጥላል።

 ግንባታው ከደረጃዎች ምድባ ኤጀንሲና ሌሎች ገለልተኛ ተቋማት የግንባታ ጥራቱ እየተፈተሸ በመከናወን ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።

በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ኩባንያ የሚገነባውና 60 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ይህ ስታዲየም ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ የሚከናወን ይሆናል።

የስታዲሙን ግንባታ በሁለት ዓመት ተኩል በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ እቅድ ተይዟል።

ምንጭ፡- ኢዜአ

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች