ኢትዮጵያ ሌሴቶን 2 ለ 1 አሸነፈች

ሰኔ 07፣2007

ለ2017ቱ የጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 10 የተደለደለችው ኢትዮጵያ ሌሴቶን 2 ለ 1 አሸነፈች፡፡

ከ80 ሺህ በላይ ተመልካች ባስተናገደው የባህር ዳር ብሄራዊ ስታዲየም በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻሉ የነበሩት ሌሴቶዎች 1 ለ 0 በመምራት አጠናቀዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ68ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ ሳልሃዲን ሰኢድ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ጨዋታው 2 ለ 1 ተጠናቋል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ መበለጣቸውን ያመኑት የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከእረፍት መልስ የተሻለ መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ባዬ ገዛኻኝና ራም ኬሎ፣ ጌታነህ ከበደንና ሽመልስ በቀለን ተክተው በመግባት ጨዋታውን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡

በስታዲዬም የተገኘው ደጋፊም 12ኛ ተጫዋች በመሆን ለቡድኑ ውጤታማነት ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ብለዋል አሰልጣኝ ዮሐንስ፡፡

የቡድኑ አማካይ የሆነው በኃይሉ አሰፋ በበኩሉ ሌሴቶዎች ከጠበቅነው በላይ ቢሆኑም ከዕረፍት መለስ ጠንክረን ተጫውተን አሸንፈናል ብሏል፡፡

በስታዲዬሙ የነበረው ዝናብ ምንም ጫና እንዳልነበረውም ጠቁሟል፡፡

ተጫዋቾቹ ባሸነፉ ቁጥር ሽልማት መዘጋጀቱን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መሪ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ የገንዘዘቡን መጠን ሳይጠቅሱ አልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁኔይዲ ባሻ በበኩላቸው በስታዲየሙ የነበረውን ድባብ አድንቀዋል፡፡

በባህር ዳር ስታዲየም የነበረው ደጋፊ ቡድኑ ሲመራም ሆነ ዝናብ ሲጥል ድጋፉን አላቋረጠም ነበር፡፡

የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው ዙሪያ ምንም መግለጫ አልሰጠም፡፡

በዚሁ ምድብ የሚገኙት አልጄሪያና ሲሸልስ ባደረጉት ጨዋታ አልጄሪያ 4 ለ 0 በማሸነፍ ምድቡን መምራት ጀምራለች፡፡

ጥንቅር ፡- ወገኔ አለማየሁና አዝመራው ሙሴ

 

Average (0 Votes)