በኢትዮጵያ አዲስ የገንዘብ ዓይነት ይፋ ተደረገ

3 Yrs Ago
በኢትዮጵያ አዲስ የገንዘብ ዓይነት ይፋ ተደረገ
አዲስ የገንዘብ ኖት

ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች ሙሉ ለሙሉ በመተካት ለግብይት የሚሆን አዲስ የገንዘብ ዓይነት መጠቀም እንደምትጀምር በዛሬው ዕለት ይፋ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ አደረጉ።

ይህም አዲሱን የ200 ብር ገንዘብ ይጨምራል። እነዚህ አዲስ የገንዘብ ዓይነቶች ለሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግን ድጋፍ፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቀልበስ ይረዳሉ።

የ5 ብር ገንዘብ ባለበት ቀጥሎ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ወደ ሣንቲም እንደሚቀየር ተገልጿል።

ለአዲሱ ገንዘብ ለህትመት 3.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

አሁን በገበያ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀየርም ተገልጿል።

አብዛኛው የመቀየር ስራዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም ነው የተገለፀው።

በአዲሶቹ የገንዘብ ዓይነቶች ላይ የተካተቱ መለያዎች አመሳስሎ ገንዘብ ለማተም የሚደረጉ ሕገ ወጥ ጥረቶችንም ለማስቀረት ያግዛሉ።

አብዛኛው የሕትመት ሥራ ተገባዶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግምጃ ቤት እንደሚገኝ እና የስርጭት ስርዓት እና ዕቅድ ተዘጋጅቶ በሚመለከታቸው አካላት አማካኝነት የሚተገበር እንደሚሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በገንዘብ ቅያሬው ሂደት የጸጥታ ማስከበር አካላት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንደሚያስፈፅሙም ነው የተጠቆመው።

ሂደቱን በበላይነት የሚያስተባብር ከብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እና ከፌደራል ፖሊስ የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት እንደሚቋቋምም ተገልጿል።

የክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ ኮማንድ ፖስት አቋቁመው ሥራውን እንዲያከናውኑም ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ገንዘቧን የሚወክል ምልክት እንዳልነበራት ይታወቃል። በቅርቡ ለብር መለያ የሚሆን አዲስ ምልክት ተዘጋጅቶ በጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top