ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ለቻይና የመከላከያ ሠራዊት የምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

1 Yr Ago
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ለቻይና የመከላከያ ሠራዊት የምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የቻይና የመከላከያ ሰራዊት የተመሰረተበትን 95ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ባስተላለፉት መልዕክት የቻይና የመከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ሉአላዊነት፣ ፀጥታና ጥቅም ከማስከበር አልፎ ለዓለማችን ሰላምና መረጋጋት እያደረገ ላለው በጎ ሚና ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል። ቻይናና ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ታሪካዊ ወዳጅነት እንዳላቸው ያወሱት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፤ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በመመስረት በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በትምህርት እና በጤና መስኮች ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ገልፀዋል። ሁለቱ ወዳጅ ሀገራት በወታደራዊ ዲፕሎማሲና ትብብር ላይ ከፍተኛ ዕድገት ደረጃ ላይ እንደደረሱ የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ አገራቱ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራም እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top