በአማራ ክልል የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን ከነበሩበት በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት ሥራዎች ተጀምረዋል”፦ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

1 Yr Ago
በአማራ ክልል የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን ከነበሩበት በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት ሥራዎች ተጀምረዋል”፦ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
በአማራ ክልል የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን ከነበሩበት በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት ሥራዎች መጀመራቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2014 ትምህርት ዘመን ሥራ አፈፃፀም እና የ2015 ዓ.ም ዕቅድ ላይ የሚመክር መድረክ በወልዲያ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተቤ ታፈረን ጨምሮ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ ክልሉ በህወሓት የተፈፀመበት ወረራ ሙሉ ትኩረቱን ወስዶ እንደነበር ገልጸው፣ በዚህም የትምህርት መስክን ጨምሮ የሁሉም ዘርፎች ሥራ መቆሙ መሥዋዕትነት ያስከፈለ ነበር ብለዋል። በወረራውም በትምህርት ተቋማት ላይ በደረሰው ከፍተኛ ውድመት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ መደረጋቸውን ተናግረዋል። የወደሙ ተቋማትን ከነበሩት በላቀ ለመገንባት በደሴ መሠረት መጣሉን ገልጸው፣ የትምህርት ሥርዓቱን በውጤታማነት ለመምራት እየተሠራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል። የትምህርት ዘመኑ በችግር ውስጥም ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር የገለጹት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተቤ ታፈረ፣ የጦርነቱ ሁለንተናዊ ጫና ለትምህርት ዘርፉ ዋና ፈተና እንደነበር አንስተዋል። የተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት ማሽቆልቆል፣ ማቋረጥ፣ በርካታ ተማሪዎች በወረራው መፈናቀል እና የ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ አጋጥመው የነበሩ ችግሮች ፈታኝ እንደነበሩም ገልጸዋል። በአጠቃላይ በትምህርት ሥርዓቱ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ የትምህርት ዘመኑ የተማሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top