ኢትዮጵያ ያለችብትን ብዙ ፈተናዎች ለማቋቋም በአንድነት መቆም ያስፈልጋል”፦ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

30/08/2022 12:53
ኢትዮጵያ ያለችብትን ብዙ ፈተናዎች ለማቋቋም በአንድነት መቆም ያስፈልጋል”፦ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በመሆኗ እነዚህን ፈተናዎች ለማቋቋ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት እንዲቆም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጥሪ አቀረበ። የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መገለጫ ሰጥተዋል። የውጭ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች ግንባር ፈጥረው ዘመቻ ከፍተውብናል ያሉት አቶ ከበደ፣ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገራቸው ሰላም ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። አሸባሪዎቹ ሸኔ፣ ህወሓት እና አልሸባብ ቡድኖች ግንባር በመፍጠር በኢትዮጵያ የሀይማኖት ግጭት እንዲስፋፋ፣ ሰዎች እንዲገደሉ እና አንዲፈናቀሉ አንዲሁም ሀብት እና ንብረት እንዲወድም ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የቀረቡለትን የሰላም አማራጮች ወደ ጎን በመተው ሕፃናትን ሳይቀር በማሰለፍ ለሦስተኛ ዙር እልቂት ማዘጋጀቱን በተመለከተ ሲናገሩ፣ “አሸባሪው ህወሓት ጦርነት የከፈተው የማሸነፍ ዓላማ ይዞ ሳይሆን ከትግራይ ሕዝብ ጥያቄ ለመደበቅ ነው” ብለዋል። አሸባሪው ህወሓት ለጀመረው ይፋዊ ወረራ መንግሥት እስካሁን ከመመከት ያለፈ የማጥቃት እርምጃ እንዳልወሰደ ገልጸዋል። መንግሥት ችግሮችን ከጦርነት ይልቅ በንግግር ለመፍታት ያለው አቋም አሁንም ፅኑ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በአንፃሩ የሽብር ቡድኑ የቀረቡለትን የሰላም አማራጮች ለመቀበል ዝግጁ አይደለም ብለዋል። በሌላ በኩል፣ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም በሩሲያ እና በዩክሬን ግጭት ምክንያት ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናም አንገቷን ቀና ማድረግ መቻሏንም ነው የገለጹት። ድርቅ በተከሰተባቸው አከባቢዎችም የብዙዎችን ሕይወት የመታደግ ሥራ መሠራቱንም አቶ ከበደ ዴሲሳ በመግለጫቸው አንሥተዋል። ለአዲሱ ዓመት እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችን በተመለከተ ደግሞ፣ የ2015 አዲስ ዓመት “ጳጉሜን በመደመር” በሚል በተለያዩ መሪ ሐሶች እንደሚከበርም ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት
ጳጉሜ 1 - የበጎ ፍቃድ ቀን፣
ጳጉሜ 2 - የአምራችነት፣
ጳጉሜ 3 - የሰላም ቀን፣
ጳጉሜ 4 - የአገልጋይነት ቀን እንዲሁም
ጳጉሜ 5 - የአንድነት ቀን ተብሎ መሰየሙን ነው ያስታወቁት።
 
 
የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የተመረጡ አጫጭር የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የቲክቶክ አካውንታችንን ይከተሉ
ግብረመልስ
Top