ለ3 ዓመታት የተጓተተውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ህንጻ ግንባታ ለማፋጠን የእርምት እርምጃ መውሰዱን የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታወቀ

1 Yr Ago
ለ3 ዓመታት የተጓተተውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ህንጻ ግንባታ ለማፋጠን የእርምት እርምጃ መውሰዱን የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታወቀ
በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በማለም በ2011 ዓ.ም ላይ ግንባታው የተጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ፕሮፌሽናል ህንጻ ግንባታ በጊዜው ባለመጠናቀቁ በመንግስት ላይ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ አስከትሏል።
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከአፍሮ-ጽዮን ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ/ ጋር የህንፃውን ግንባታ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት በሶስት ዓመት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ውል ተይዞ እንደነበር የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዘሃራ አብዱልሃዲ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ገልፀዋል።
ይሁንእንጂ ተቋራጩ ኩባንያ በነበረው ደካማ አፈጻጸም በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 22% መስራት የነበረበት ቢሆንም መስራት የቻለው 6% ብቻ በመሆኑ በግንባታው ከፍተኛ መጓተት መፈጠሩን አመለክተዋል፤ በመሆኑም ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጎ የእርምት እርምጃ መወሰዱን ነው ኢንጅነሯ የጠቆሙት።
በአሁኑ ወቅት የዚህን ፕሮጀክት ግንባታ ስራ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ቀደም ሲል በተለያዩ ፕሮጀክቶች ስራዎች ላይ ከነበረው የተሻለ የስራ አፈጻጸም በመነሳት ኦቪድ ግሩፕ ከተባለ አገር በቀል ድርጅት ጋር በቀጥታ ውል ተገብቶ የግንባታ ስራው በመፋጠን ላይ እንደሚገኝም የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታውቋል።
አሁን ላይ ኢቢሲ ሳይበርም ግንባታው በፍጥነት እየተካሄደ ስለመሆኑ በቦታው ቅኝት አድርጎ አረጋግጧል።
 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ፕሮፌሽናል ህንጻ ግንባታን በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ አዲሱ ተቋራጭ ኩባንያ ኦቪድ ግሩብ በ2.9 ቢሊዮን ብር ገንብቶ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን የጽ/ቤቱ ኃላፊ ኢንጂር ዘሃራ አብዱልሃዲ አመልክተዋል።
በአዲሱ ውል መሰረት ከ3 ዓመታት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ፕሮፌሽናል ህንጻ ግንባታ በ6 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ላይ 2B+G+11 ከፍታ እንዲኖረው ተደርጎ ነው በመገንባት ላይ ያለው።
መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት በቅርበት ከተከታተሉትና ድጋፍ ካደረጉ በተባለው ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ግንባታውን በበላይነት እየተቆጣጠረ ያለው የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አመልክቷል።
በመስፍን ገብረማርያም

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top