አፍሪካ በጤና እና በምግብ ችግሯን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው - ሙሳ ፋኪ ማሀማት

1 Yr Ago
አፍሪካ በጤና እና በምግብ ችግሯን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው - ሙሳ ፋኪ ማሀማት

አፍሪካ በጤና እና በምግብ ችግሯን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን አፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት ተናገሩ።

42ኛው የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ ተጀምሯል።

አፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት አፍሪካ በቱርክ እና  ሶሪያ በደረሰው ተፈጥሯዊ አደጋ ኀዘናቸውን በመግለፅ ስብሰባውን አስጀምረዋል።

ሊቀመንበሩ የአፍሪካ ጤና እና ሥነ-ምግብ ቁልፉ የኅብረቱ ሥራዎች አድርጋ በቀዳሚነት እየሠራች መሆኑን ገልፀዋል።

የአፍሪካ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል እና የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ መቋቋማቸው ይህን ጥረቷን ለማሳካት ብሎም ከጥገኝነት ለመላቀቅ እንደሚያስችላት ጠቅሰዋል።

በጤና አጠባበቅ እና በሥነ-ምግብ ራስን ለመቻልም አገራት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ ረገድ አፍሪካ የንግድ ግብይትን ለማሳለጥ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራም ለማፋጠን እየተሠራ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ ያላትን ሀብቶችን አሟጥጣ ለመጠቀም፣ ዲጂታላይዜሽንን ለማፋጠን፣ የዕውቀት ሽግግር ለመፍጠር  በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።

በአህጉራዊ ሰላም እና ደህንነት ረገድ ደግሞ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ የመፍታት ማዕቀፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት በኅብረቱ መሪነት  ሰላም የማረጋገጥ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ጣልቃገብነት የችግሮቹ መባባስ እንጂ መፍትሔ እንደማይሆን ገልጸው፣ በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሊቢያ፣ በጊኒ ቢሳው፣ በሶማሊያ፣ በማሊ፣ በቡርኪናፋሶ የተከሰቱ የሰላም ችግሮች እንደሚፈቱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በድርድር እና በሌሎች አማራጮች ወሳኝ ሚና ስለመጫወቱ አንስተዋል።

ሊቀመንበሩ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፍትሔ በሚለው መርሕ አህጉራዊ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈቱ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ጥረቶችንም አባላቱ እና አጋር አገራት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በወጣቶች እና ሴቶች ፋይናንስ አካታችነት ረገድ በተለይም የ2063 የአፍሪካ አጀንዳ ዕውን ለማድረግ በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ተለዋጭ በሆነው ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካ አፍሪካ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ላይ የተመሠረተ የባለብዙ ወገን ትብብሮችን እንደምታጠናክር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ምክር ቤቱ በ45ኛው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች መደበኛ ስብሰባ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል።

ለአብነትም በኅብረቱ እና ተጠሪ ተቋማቱን ዓመታዊ ሪፖርት፣ የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ ማቋቋም ሂደት፣ የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል ሥራ ማስጀመር ሪፖርት፣ የ2022 የአፍሪካ ሥነ-ምግብ ፍኖተ ካርታ ሪፖርት ያደምጣል።

እንዲሁም የ2013 የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ማፋጠን መሪ ቃልን የማፅደቅ ጉዳዮች እንደሚወያይ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ምርጫም እንደሚደረግም ይጠበቃል።

የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት የአባል አገራትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ያቀፈ ነው።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top