ቦርዱ በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ አፈፃፀም ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሄድ አዘዘ

1 Yr Ago
ቦርዱ በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ አፈፃፀም ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሄድ አዘዘ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ ሂደትን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ አዳጋች ሁኔታ መፈጠሩን በመጥቀስ በሂደቱ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ አዟል፡፡
ምርጫ ቦርድ በሂደቱ ቁጥራቸው ጥቂት በማይባል የምርጫ ጣቢያዎች በሕጉ መሠረትና አግባብነት ባላቸው መመሪያዎች እንደ ከባድ የአሠራር ጥሠት የሚቆጠሩ ተግባራት መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡
በመሆኑም የጥሰቶቹን ስፋት እና የሚሸፍኗቸውን ጣቢያዎች በተመለከተ ቦርዱ ተጨማሪ ምርመራ እንዲከናወን አዟል፡፡
የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚሰጥም ቦርዱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቦርዱ በመግለጫው በዞኑ የህዝበ ውሳኔ አፈፃፀም ሂደት የታዩ ጥሰቶችን እንደሚከተለው ዘርዝሯል፥
1. በመራጮች ምዝገባ ወቅት በመዝገቡ ላይ የሠፈረው የመራጮች ፊርማ በድምፅ መስጫ ቀን ከተፈረመው ፊርማቸው ጋር የተለያየ መሆን፣
2. በምዝገባ ወቅት በጽሑፍ ፊርማ የተፈረመ በድምፅ መስጫ ቀን በጣት አሻራ የተፈረመ የመራጮች ዝርዝር በመዝገቦቹ ላይ መታየቱ፣
3. በምዝገባ ወቅት በጣት አሻራ የተፈረመ በድምፅ መስጫ ቀን በጽሑፍ ፊርማ የተፈረመ የመራጮች ዝርዝር በመዝገቦች ላይ መታየቱ፣
4. በመራጮች መዝገብ ላይ ለተመዘገቡ የተለያዩ መራጮች (በምዝገባ ወቅትም፣ በድምፅ መስጫ ቀንም) አንድ ዓይነት ፊርማ ተፈርሞ መገኘቱ፣
5. በመራጮች መዝገብ ላይ ከሚጠበቀው በላይ ብዛት ያለው የጣት አሻራ ምልክት (በመራጮች ምዝገባ ወቅትና በድምፅ መስጫ ቀን) የተደረገ መሆኑ፣
6. በመራጮች መዝገብ ላይ የመራጮቹ መረጃ ተሞልተው ፊርማቸው በጽሑፍም ሆነ በአሻራ አለመሥፈሩ፣
7. ከ18-50 ዕድሜ ያላቸውና ማንበብና መጻፍ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ በርካታ መራጮች በአሻራ እንደፈረሙ መታየቱ፣
8. በመራጮች ምዝገባ ቀን በአሻራ ተፈርሞ በድምፅ መስጫ ቀን ፊርማ መፈረም ባለበት ቦታ ላይ የራይት ምልክት መደረጉ፣
9. በመራጮች መዝገብ ላይ ስለመራጮቹ ሊሠፍሩ የሚገቡ የመራጮች መረጃ በአግባቡ አለመሞላታቸው፤
ከድምፅ አሰጣጥና ውጤት ጋር በተያያዘ የታዩ የአሰራር ጥሰቶች ደግሞ፥
1. ጥርጣሬን በሚፈጥር ሁኔታ በበርካታ ጣቢያዎች በመራጭነት የተመዘገቡና በሕዝበ ውሣኔው ቀን የመረጡ የመራጮች ብዛት ዕኩል ሆኖ መታየት፣
2. የውጤት ማሳወቂያ ቅጽ ላይ የማይፈቀዱ የዕርምት ሥራዎች መሠራቱና በሠነዶቹ ላይ ከፍተኛ ሥርዝ ድልዝ መታየቱ፣
3. የድምፅ መስጫ ወረቀት ብዛት፤ ከተመዘገቡና ድምፅ ከሰጡ መራጮችና ቁጥር አለመታረቅ፣
4. የውጤት መግለጫ ቅጾችና የመራጮች መዝገብ ላይ ምርጫ አስፈጻሚዎች ፊርማቸውን በሠነዶቹ ላይ አለማሥፈራቸው፣
5. ብዛት ያላቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በአንድ ላይ ታጥፈው በድምፅ መስጫ ሣጥን ውስጥ ታጭቀው መገኘታቸው፣
6. በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ለመስጠት ለተሠለፉ መራጮች ጊዜያዊ መታወቂያ ወረቀት በአካባቢ አስተዳደር አካላት መታደል መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top