የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

1 Yr Ago
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
 
ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በትምህርትና ስልጠና ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ሲሆን በስራ ላይ ያለው ፖሊሲ ላለፉት 28 ዓመታት ማሻሻያ ሳይደረግበት መቆየቱ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ከማፍራት፤ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን ከማበረታታት ፣ እንዲሁም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን መዘንጋቱ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ሰፊ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ በመሆኑም ለሁሉም ህጻናትና ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት ማዳረስ፤ ትውልዱን ባለብዙ ልሳን እና ተወዳዳሪ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት፣ ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚያስችል የዘርፉን ዓለም አቀፋዊ ለውጦች መሠረት ባደረገ መልኩ የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ግብ ያደረገ ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ከዛሬ ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመደንገግ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻ ሆነው ስለአካዳሚክ ስራዎቻቸው በራሳቸው መወሰን እንዲችሉ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራ የዳበረ ዕውቀት የሚገኝባቸው ተቋማት እንዲሆኑ፤ ሕብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚያነባቸው፤ የራሳቸውን የገቢ ምንጮች በማስፋት በሂደትም በራሳቸው በጀት የሚተዳደሩ እንዲሆኑ ማስቻልን ታሳቢ ያደረገ ቀስ በቀስ በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ላይ የሚተገበር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3 ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ በከፍተኛ የመንግስት ትምህርት ተቋማት እና በማስተማሪያ ሆስፒታሎች የሚሰሩ የአካዳሚክ ቴከኒክ ረዳቶችን ተጣባርና ሀላፊነት እንዲሁም ጥቅማ ጥቅም ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ሲሆን በከፍተኛ የመንግስት ትምህርት ተቋማት ውስጥ በላብራቶሪዎች፣ በኢንዱስትሪዎች፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሞያዎችን መብትና ግዴታዎች እንዲሁም ሊሟሙላቸው የሚገቡ ጥቅሞችን በህግ መደንገግ የስራ ተነሳሽነትን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ለከፍተኛ ትምህርት ተልዕኮ ስኬት ድርሻው የጎላ መሆኑ ስለታመነበት ለከፍተኛ ትምህርት ሁለንተናዊ እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሰራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው በከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በምርምር ተቋማት እና በኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመተባበር በእውቀትና በክህሎት የጎለበተ፣ ገበያው የሚፈልገውን የሠለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ያደረጓቸው ጥረቶች በተግዳሮቶች የታጠሩ እና የሚጠበቀውን ውጤት ያላሳኩ በመሆኑ ይህንን ትስስር በህግ ማእቀፍ ከፍ በማድረግ ከኢንዱስትሪው ጋር የሚመሰረተው ትስስር የዕውቀት ሽግግርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን፤ ለብዝሃ ኢኮኖሚ ኢድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል ከሆኑም በላይ ችግር ፈቺ ምርምር እንዲያከናውኑ፣ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲገኙ የሁሉንም ባሊድርሻ አካላት መብትና ግዴታዎች መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top