የዓድዋ ድል በዓል ትልቅነቱን በሚመጥን መልኩ ለማክበር ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል፡- የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር

1 Yr Ago
የዓድዋ ድል በዓል ትልቅነቱን በሚመጥን መልኩ ለማክበር ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል፡- የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር
የዓድዋ ድል በዓል ትልቅነቱን በሚመጥን መልኩ ለማክበር ሰፊ ዝግጅት መደረጉን የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።
የመታሰቢያ በዓሉን በሁሉም ክልሎችና ከተሞች ወጥነት ባለው እና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሃይማኖት አለማየሁ ለኢቢሲ ሳይበር ገልጸዋል።
127ኛውን የዓድዋ ድል በዓል መከላከያ ሚኒስቴር ኃላፊነት ወስዶ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እንዲያከብረው መወሰኑ ከዚህ በፊት ከነበሩ የዓድዋ ድል አከባበሮች ልዩ እንደሚያደርገው ስራ አስፈፃሚዋ ጠቅሰዋል።
በዚህም መሰረት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ ከጥንታዊ ኢትዮጵያ አርበኞች፣ ከፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በህብረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
‘የዓድዋ በዓል እንደሃገር ወጥ በሆነ መልኩ መከበር አለበት’ በሚል በመንግስት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት በበዓሉ አከባበሩ ዙሪያ እቅድ ተዘጋጅቶ በመከበር ላይ ይገኛል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እና ከዐቢይ ኮሚቴው በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት በበዓሉ ዋዜማ የካቲት 22 የሚደረጉ የተለያዩ የፓናል ውይይቶችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ባለፈም በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ አውደ ርዕዮች መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት ስራ አስፈፃሚዋ፤ በሚኒስቴሩ አዘጋጅነት ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ እንግዶች የሚገኙበት አውደ ርዕዩ በዛሬው ዕለት እንደሚካሄደም ተናግረዋል።
በመከላከያ ሚኒስቴር ይፋ በተደረገው መሰረት በበዓሉ ዕለት በሚኒሊክ አደባባይ በሚኖረው ስነ-ስርዓት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠው በመከላከያ ማርሽ ባንድ የታገዙ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ወ/ሮ ሃይማኖት ገልጸዋል።
በዓሉ በሚኒሊክ አደባባይ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ከተከበረ በኋላ ወደ ዓድዋ ድልድይ በማቅናት በወቅቱ አባቶች ድልድዩን እንዴት ተሻግረው ወደ ጦርነቱ እንደዘመቱ የሚያሳይ ትርኢት እንደሚቀርብም ተገልጿል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ በመስቀል አደባባይ በተሰናዳው ዝግጅት የሃገር መከላከያ የሚያቀርባቸው ወታደራዊ ትርኢቶች እና ሰልፎች እንደሚኖሩ የገለጹት ስራ አስፈፃሚዋ፣ ብዙ ሰዎች የሚሳተፉበት የአደባባይ ስነ ስርዓት እና የአድዋ ጀግኖች የሚዘከሩበት ሰፊ መርሃግብር መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
በይስሃቅ ታሪኩ
 

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top