ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ያከናወናቸውን ተግባራት ለምክር ቤት አቀረበ

1 Yr Ago
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ያከናወናቸውን ተግባራት ለምክር ቤት አቀረበ
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ለምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ለባለድርሻ አካላት ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡
 
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ከየካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የራሱን ጽ/ቤት ከማቋቋም አንስቶ የምክክሩ ሂደት ተዓማኒ፣ ግልጽ፣ አሳታፊ እና የህብረተሰቡን ባለቤትነት ያረጋገጠ እንዲሆን በርካታ ቁልፍ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
 
በዚህም ኮሚሽኑ የምክክር ተሳታፊዎችን ለመለየት፣ አወያዮችንና አመቻቾችን ለመመልመል፣ ስልጠና ለመስጠት፣ የመወያያ አጀንዳዎችን ለማሰባሰብ እና አጀንዳዎችን ለመቅረፅ የሚያስችሉ የተለያዩ መመሪያዎችን ጨምሮ ግልጽ የአሠራር ስርዓቶችን የማዘጋጀት አንኳር አንኳር ሥራዎች መሠራታቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
 
ሀገራዊ ምክክሩ እንዲካሄድ በመንግስት፣ በክልሎችና በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍና ፍላጎቶች መኖራቸውን በመልካም አጋጣሚነት አንስተዋል፡፡
 
በዋናነት ኮሚሽኑ የመጀመሪያና የሁለተኛ ምዕራፍ ስራዎቹን አጠናቆ የሶስተኛውን ምዕራፍ ሀገራዊ ምክክሩን የማስጀመር ሥራውን በግንቦት ወር እንደሚጀምርም ነው የገለጹት፡፡
 
የምክክሩ ሂደት ሁሉን አሳታፊ እና ‘’በምክክሩ አልተሳተፍኩም ነበር’’ የሚለው ቅሬታ እንዳይነሳ በአጀንዳ ማሰባሰቡ ላይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች እና አደረጃጀቶችን ያካተተ እንዲሆን በጥንቃቄ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
 
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክር የማድረጉ ጉዳይ ሀገርን የማሻገር እና በመንግስት በኩል በበጀት ዓመቱ መከናወን አለባቸው በሚል በአቋም ከተያዙ ሀገራዊ አጀንዳዎች ውስጥ ዋነኛው መሆኑን መግለፃቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top