በወር እስከ 2 ሚሊዮን ብር ለወገኖቹ ሕይወት መቃናት ድጋፍ የሚያደርገው ወጣት

1 Yr Ago
በወር እስከ 2 ሚሊዮን ብር ለወገኖቹ ሕይወት መቃናት ድጋፍ የሚያደርገው ወጣት
ማስተር አብነት ከበደ
የበጎ ተግባር እና መልካም ሥራ ላይ መሳተፍን ነፍሱ ትወዳለች፣ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት በጎ ተግባራት ማከናወን ገና በልጅነቱ ከቤተሰቡ የወረሰው መልካም ተግባር ነው።
ማስተር አብነት ከበደ ዕድሜው ገና ወጣት ቢሆንም የሚያከናውናቸው ሰብዓዊ ተግባራት አጃኢብ የሚያስብሉ ናቸው።
ወጣቱ በጎ አድራጊ ማስተር አብነት ከበደ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎችን መርዳት ይወዳል፣ የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀም የሚያዘወትረው ማስተር አብነት በየወሩ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ድረስ ድጋፍ በማድረግ የተሰበሩ ልቦችን ይጠግናል።
ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለሚያከናውናቸው በጎ ተግባራት በመሣሪያነት ይጠቀማል፤ የ30 ዓመቱ ወጣት ማስተር አብነት “ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሚሊዮኖች ጋር በቀላሉ እንዲደርስ ጠቅሞኛል” ብሏል።
“በዚህም የተነሣ በጎ አድራጊዎች እና በድህነት ምክንያት ልባቸው የተሰበሩ ሰዎች ድልድይ እንድሆን ምክንያት ሆነውኛልም” ይላል።
የሚያከናውናቸውን በጎ ተግባራት ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ማጋራት ከጀመረ 6 ወራትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከዚያም በፊት ሰዎችን ከመርዳት ቦዝኖ እንደማያውቅ ለኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ በሰጠው ቃለ ምልልስ ገልጿል።
እንደስሙ ተምሳሌታዊ በጎ ተግባራትን የሚከውነው አብነት የመራብን እና የመጠማትን ስሜት፣ የማግኘትን እና የማጣትን ሕመም በተግባር ማየቱን ይገልጻል።
ነገሮች ሳይሳኩ በሕይወት ውጣ ወረዶች ውስጥ እንኳ ሆነን ሰዎችን የመርዳትን አስፈላጊነት የሚናገረው አብነት፣ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ክልል ከምባታ ጠንባሮ ዞን ሲሆን ሰውን መርዳት ገና በልጅነቱ የተማረው ደግሞ ከቤተሰቡ እንደሆና ይናገራል።
በኢትዮጵያ ገጠር እና ከተማ አካባቢዎች መኖሪያ ቤታቸው ፈርሶባቸው፣ መጠለያ አጥተው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከ18 በላይ ቤቶችን ሠርቶ አስረክቧል።
በተፈጥሮ ችግር ምክንያት በደረታቸው የሚሄዱ ሕፃናት እና ቤት ውስጥ ለመቀመጥ የተገደዱ አባቶችን ቀርቦ በመረዳት ወገኖቹን አስተባብሮ በማሳከም፣ ዊልቸር ገዝቶ በመስጠት ድጋፍ አድርጓል።
በአሁን ጊዜ፣ በቦረና በተከሰተው ድርቅ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአደጋ የተጋለጡ ሲሆን ከ604 ሺህ በላይ ወገኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የአደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ያወጠው መረጃ ያመለክታል።
መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጨምሮ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዕርዳታ በማሰባሰብ ዜጎችን ለመታደግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፤ ወጣት አብነትም በስፍራው በመገኘት ለወገኖቹ የሚጠበቅበትን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
“ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” የሚለው ወጣት አብነት፣ ሰዎችን በመርዳት ሂደት መንፈሳዊ እርካታን እና አዕምሯዊ እረፍትን እንደሚያገኝ ገልጿል።
በመንገድ ዳር የወደቁ ፣ ጧሪ እና ረዳት የሌላቸውን ወገኖችን በመርዳት፣ ሆስፒታል ጠያቂ የሌላቸውን ወገኖች በመጠየቅ፣ ቤት ፈርሶባቸው መጠለያ አጥተው መሄጃ ላጡ ወገኖች መኖሪያ ቤት በመሥራት እና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በመድረስ ለወገን ደራሽነቱን በተግባር አሳይቷል፤ እያሳየም ይገኛል።
ወጣቱ ርህሩህ እና መልካም ልብ ካላቸው ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚያሰባስበውን ድጋፍና ዕርዳታ በታማኝነት ለተጎዱ ወገኖች በማድረስ መልካም እና አርአያ ወጣት መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል።
በመሐመድ ፊጣሞ

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top