ባለሀብቶች በ‘ድሮን’ ቴክኖሎጂ ላይ መሰማራት ይችላሉ፦ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን

1 Yr Ago
ባለሀብቶች በ‘ድሮን’ ቴክኖሎጂ ላይ መሰማራት ይችላሉ፦ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን
ባለሀብቶች ከአቪዬሽን ኢንቨስትመንት በተጨማሪ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ቴክኖሎጂ ላይ መሰማራት እና የድሮን አገልግሎት መስጠት እንዲሁም በኤሮ ስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ላይ መሥራት እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ለኢፕድ እንደገለፁት፣ በቀጣይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን መቆጣጠራቸው አይቀርም።
ይህን በተመለከተ የድሮን አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን ድሮኖችን እዚህ እስከመገጣጠም ድረስ መሠራት አለበት። ሰው አልባ አውሮፕላን የሚገጣጥሙት አካላት ካሉም ሊደገፉ ይገባል ብለዋል።
ባለሀብቶች በድሮን ቴክኖሎጂ መሰማራት ከፈለጉም፣ ድሮን መገጣጣም እና ማምረት ውስጥ ቢገቡ አዋጭ ስለመሆኑም መክረዋል። በአሁኑ ወቅት ሰው አልባ አውሮፕላኖች የዓለምን ቀልብ የሳቡ እና የፉክክር መስክ በመሆናቸው በዚህ ላይ በፍጥነት መግባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የማምረት ፈቃድ ሲሰጥ ከደኅንነት አኳያ ትልቅ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ ይህን በተመለከተ በባለሥልጣኑ በኩል ‘ሬጉሌሽን’ ወጥቷል።
በተጨማሪም ከሚመለከታቸው የደህንነት ተቋማት ጋር ውይይት በመደረጉ እንደየድርሻቸው ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። ይሁንና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በዋናነት ተቆጣጣሪ ይሆናል ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ባለሀብቶች በኤሮ ስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ማምረት መሰማራት የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል። ከአውሮፕላን አምራቾች ጋር ትብብር በመፍጠር ለእነርሱ የሚሆኑ ግብዓቶቸን እና መለዋወጫዎችን ማቅረብ ይችላሉ። ባለሀብቶች ወደዚህ ዘርፍ በሰፊው ከገቡበት ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ያመጣሉ። በአውሮፕላን ጥገና መሰማራት የሚፈልጉ ካሉም አማራጮች መኖራቸውን እና ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ባለሀብቶች፣ ከተማ መስተዳድሮች እና ክልሎች በኤርፖርት ልማት ላይ የመሳተፍ ዕድል እንዳላቸው የገለጹት አቶ ጌተቻው፤ ቀደም ሲል በዚህ ላይ ለመሳተፍ ገፍቶ የመጣ አካል አለመኖሩን አብራርተዋል። ይህ ሥራ የመንግሥት ብቻ ነው የሚል ግምትም ነበር። ሆኖም ከአሁን በኋላ የግል ባለሀብቶች ከተማ አስተዳደሮች፤ የክልል መስተዳድሮች እና የፌዴራል መንግሥት በጋራ የሚሰሩት ሥራ መሆኑን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 13 የግል የአየር መንገዶች መኖቸራውንና ይህም በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ የበለጠ ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
መንግሥት ለጄኔራል አቪዬሽን ትኩረት መስጠቱንና እንደ ሀገርና መንግሥት የሚፈልገው ኢኮኖሚውን የሚደግፍ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ማስቻል ነው። በአሁኑ ወቅት አሳሳቢው ጉዳይ አገልግሎቱ በማን በኩል ይሰጥ የሚለው ሁለተኛ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።
በአቪዬሽን መስክ ኢንዱስትሪውን ለማጠናከር የኢትዮጵያን አየር መንገድ ማጠናከር በጣም ስትራቴጂክ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ አሁን ባለው ሁኔታ የአየር ትራንስፖርት በኢትዮጵያ በተለይም በአፍሪካ በጣም ያልተነካ ዘርፍ ነው። ገበያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በላይ ነው ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top