በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር ያልተገባ ተግባር በፈፀሙ የፖሊስ አባላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወሰደ

1 Yr Ago
በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር ያልተገባ ተግባር በፈፀሙ የፖሊስ አባላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወሰደ
በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር ያልተገባ ተግባር በፈፀሙ የፖሊስ አባላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።
በአዲስ አበባ የአድዋ ድል በዓል ሲከበር ያልተገባ ተግባር በፈፀሙ የፖሊስ አባላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንና ሌሎች የምርምራ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል።
ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የዓድዋ ድል በዓል አከባበር በሰላም መጠናቀቅ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለነበራቸው ጉልህ ድርሻም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል።
የዓድዋ ድል በዓል በተከበረበት እለት የመዲናዋን ሰላም ለማናጋት ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 878 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ከእነዚህ መካከልም 557ቱ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸው መረጋገጡም ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርና የፀጥታና ደኅንነት ግብረ-ኃይል አባል ጌቱ አርጋው፤ በከተማዋ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ለኢዜአ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር ያልተገባ ተግባር በፈፀሙ የፖሊስ አባላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን እና ሌሎች የምርምራ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፀጥታና ደኅንነት ግብረ-ኃይሉ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ በየካቲት ወር የተካሄዱ ሀገራዊና አህጉራዊ ትላልቅ ኩነቶችና በዓላትን በሰላም እንዲጠናቀቁ ማድረጉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ለበዓላቱና ለኩነቶቹ በሰላም መጠናቀቅ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
127ኛው የዓድዋ ድል በዓል ደማቅ በሆነ መንገድ በሰላም ተጠናቆ መንገዶች ለተሽከርካሪ ክፍት መሆን ሲጀምሩ በተለይ በምኒልክ አደባባይ ችግሮች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።
ሰላም የማይፈልጉ ጥቂት ኃይሎች የበዓሉን አውድ ለመቀየርና የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር መሞከራቸውን አንስተዋል።
ሆኖም የፀጥታና ደኅንነት ግብረ-ኃይሉ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ችግሮችን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።
በምኒልክ አደባባይና በሌሎች አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ ለማድረግ የሞከሩ 878 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ነው ያነሱት ኮሚሽነሩ፣ በተደረገው ማጣራትም በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል 557ቱ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል።
በዕለቱ ችግር የፈጠሩ ቡድኖች በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ምዕመን መስለው በመግባትና በዙሪያው በፀጥታ ኃይሉ ላይ ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቅሰው፤ በተቀናጀ መንገድ የከተማዋን ሰላም ለማናጋት አቅደው የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ደርሰንበታል ብለዋል።
በዕለቱ በተተኮሰ ጥይት የአንድ ግለሰብ ሕይወት ማለፉን ጠቅሰው፤ ምርመራና የማጣራት ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በፈረስ ላይ የነበረ ግለሰብ ላይ ያልተገባ ድርጊት በፈጸመው የፖሊስ አባል ላይም ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።
በአራዳ አካባቢ ንብረት የማውደምና የመዝረፍ ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም በጸጥታ ኃይሉ ብርቱ ጥረት መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።
በዕለቱ 16 የፖሊስ አባላት ቀላልና ከባድ ጉዳት ሲደርስባቸው ሦስት አውቶቡሶችና አንድ አምቡላንስም መሰባበራቸውን አንስተዋል።
በሌላ በኩል፣ በትላንትናው ዕለት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከ100 በላይ የባጃጅ አሽከርካሪዎች በከተማዋ ውስጥ የተከለከሉ ስፍራዎች ገብተን እናሽከረክራለን በማለት መንገድ በመዝጋትና ድንጋይ በመወርወር ችግር ለመፍጠር እንደሞከሩ አንስተዋል።
በዚህም የአካባቢውን የትራፊክ ፍሰት የማስተጓጎል፣ በፖሊስና ሰላማዊ ሰዎች እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረው፤ የፀጥታ ኃይሉ ችግሩን የፈጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
የፀጥታና ደኅንነት ግብረ-ኃይሉ የከተማዋንና የነዋሪዎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top