ኢትዮጵያ የ’ሆርን ኦፍ አፍሪካ ኢኒሺዬቲቭ’ ሊቀ-መንበርነትን ከኬንያ ተረከበች

1 Yr Ago
ኢትዮጵያ የ’ሆርን ኦፍ አፍሪካ ኢኒሺዬቲቭ’ ሊቀ-መንበርነትን ከኬንያ ተረከበች
2015 ኢትዮጵያ ለአንድ ዓመት የሚቆየውን የሆርን ኦፍ አፍሪካ ኢኒሺዬቲቭ የ2023 ሊቀ-መንበርነትን ኃላፊነት ከኬንያ ተረክባለች።
የኢኒሺዬቲቩ አባል አገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች 15ኛ ጉባኤውን ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ አካሄዷል።
ሚኒስትሮቹ እ.አ.አ በ2022 የኢኒሺዬቲቩ የስራ እንቅስቃሴ እና ተግባራት ገምግመዋል።
የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግና የዲጂታል ዘርፉን በማጎልበት ቀጣናዊ ትስስር እና ትብብርን ለማጠናከር በተወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ ውይይት ማድረጉ ተገልጿል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎችን ጨምሮ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያጋጠሙ ባሉ ክስተቶች ዙሪያም ሚኒስትሮቹ ሀሳብ መለዋወጣቸው ተነግሯል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ስብሰባውን በበይነ መረብ አማካኝነት መሳተፋቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አጋር አካላት በአፍሪካ ቀንድ የቆላማ አካባቢዎች ያጋጠመውን የድርቅ ተጽዕኖ ለመቋቋም በውሃ፣ ግብርናና የእንስሳት ሀብት ዘርፎች እያደረጉት ላለው የፋይናንስ ድጋፍ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኬንያ የፋይናንስ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ንጁጉና ኑዱንጉ ሊቀ-መንበርነታቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ወርቃለማሁ ደስታ አስረክበዋል።
በርክክቡ ስነ ስርዓት ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በቀጣናው ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር መደጋገፍና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የሆርን ኦፍ አፍሪካ ኢኒሺዬቲቭ እ.አ.አ 2019 ማብቂያ በአፍሪካ ቀንድ የፋይናንስ ሚኒስትሮች የተቋቋመ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top