ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ስኬታማነት ብሪታንያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገለፀች

1 Yr Ago
ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ስኬታማነት ብሪታንያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገለፀች
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የብሪታኒያ የልማት እና አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሪው ሚሸልን በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።
በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ በልማት ትብብር ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላቸው ያስታወሱት አቶ ደመቀ፣ ይህ ግንኙነት መጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በወቅታዊነትም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ በማድረግ ረገድ ተግራዊ እየሆኑ ስላሉ እርምጃዎች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፣ የስምምነቱ የእስካሁን ሂደት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተናግረዋል።
በግጭቱ ወንጀል በመፈፀም የሚጠረጠሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግም የሽግግር ፍትህ ስርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቶ ደመቀ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ ተግባር በአሁኑ ወቅት በጦርነት እና በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በብሪታኒያ የልማትና የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሪው ሚሸል በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን በመንግስት በኩል የተወሰደውን እርምጃ እና የታየውን ቁርጠኝነት አገራቸው እንደምታደንቅ ገልፀዋል።
ለስኬታማነቱም ሀገራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ነው ያረጋገጡት።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት ከድርቅና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ያጋጠማትን ፈተና ብሪታኒያ እንደምትገነዘብ በመጠቆም ለዚህ የሚሆን ድጋፍ ከረድኤት ድርጅቶችና ከሌሎች አለማቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን እንደሚደረግ ገልፀዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ በሁለትዮሽ እና በሌሎች የትብብር መስኮችም ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ውይይት ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top