…ባንሄድ ይሻላል! በማንኛውም ዕድሜ ክልል ላይ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚከሰት የባህርይ መለወጥ…

5 Mons Ago 1534
…ባንሄድ ይሻላል! በማንኛውም ዕድሜ ክልል ላይ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚከሰት  የባህርይ መለወጥ…
በአስተሳሰብ ስሜት እና በተግባር ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ሀዘን ውስጥ የሚከት ገለልተኛና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሰዎች ላይ ይስተዋላል። እንዲህ ያለው ሁነት በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች ላይ ይፈጠራል።
 
በዚህ ስሜት የተነሳ ብዙ ወጣቶች “ብንሄድ ይሻላል” እያሉ በለጋ እድሜያቸው ተቀጥፈዋል።
 
እኛ ግን “ባንሄድ ይሻላል” ስንል ስለዚህ ስሜት መቃወስ እና መፍትሄው ላይ ባለሞያ አናጋግረናል።
 
ግን ለመሆኑ ይህ ስሜት ምንድነው?
 
ይህማ ይላሉ የህፃናት እድገት እና የሥነ ልቦና ባለሞያዋ ዶ/ር ቱሚ ጌታቸው ድባቴ ወይም የስሜት መረበሽ አልያም ከልክ ያለፈ ጭንቀት ነው።
 
“ጭንቀት ወይም ድባቴ በማንኛውም ዕድሜ ክልል ላይ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚከሰት የባህርይ መለወጥ ሲሆን ህመም ነው ለማለት ግን የሀኪም ምርመራ ያስፈልገዋል” ነው የሚሉት ዶ/ር ቱሚ። ይህ ማለት ግን የባህርይ መለዋወጥ ሁሉ ድባቴ ነው ማለት እንዳልሆነ ገልፀዋል።
 
ባለሞያዋ እንደሚሉት አንድ ሰው በድባቴ ህመም ስር እንዳለ ለማወቅ ምልክቶች አሉ። እነዚህም፦
 
በተከታታይ የሚከሰት ከፍተኛ ድብርት፣ ምክንያት የሌለው የባዶነትና የሀዘን ስሜት፣ በምንም ነገር ደስታ ማጣት (ከዚህ በፊት ደስተኛ በሚያደርጉ ነገሮች ጭምር)፣ ያልታሰበ የሰውነት ክብደት መጨመር ወይም መቀነስ፣ ምንም ሳይሰሩ መድከምና አቅም ማጣት፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ ጥቅም የለኝም የሚል ስሜት፣ በነገሮች ሁሉ እኔ ነኝ ጥፋተኛ ብሎ ማሰብና መጨነቅ፣ ሃሳብን ለመሰብሰብ መቸገር፣ መርሳት እንዲሁም ራስን የማጥፋት ፍላጎት ማሳደር ናቸው።
 
አንድ ሰው ቢያንስ ለሁለት ሳምንት በተከታታይ እንደዚህ አይነት ስሜቶች ካስተናገደ እና ከእለት ተእለት እንቅስቃሴው ከተገደበ የድባቴ ህመም ሊሆን ስለሚችል ወደ ህክምና ቦታ ማቅናት እንደሚገባ ነው ዶ/ር ቱሚ የገለጹት።
 
“ብዙዎቻችን ስለድባቴ የምንሰማው መጨረሻውን ነው። የሆነ ሰው እራሱን አጠፋ ሲባል ነው።” ያሉት ባለሞያዋ ይህ ግን በህክምና ከመረዳት መዘግየት የሚመጣ ውጤት ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
 
“የሆርሞንና የሰውነት ቅርፅ ለውጥ ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር ለመግባባት መቸገር አለ” የሚሉት ባለሞያዋ በተለምዶ አፍላ እድሜ “fire age” የሚባለው የእድሜ ክልል የባህርይ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ተፅዕኖ ለድባቴ ህመም መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።
 
ወላጆች እነዚህን ምልክቶች በልጆቻቸው ላይ ከተመለከቱ ልጆቻቸውን ሊቀርቧቸው ሊያናግሯቸው አልያም የህክምና ባለሞያ ጋር ወስደው ሊያማክሩ ይግባል ነው ያሉት ባለሞያዋ።
 
ሰው ያለውን አቅምና ችሎታ እንዳይጠቀም የሚያደርገው ድባቴ ችላ ሊባል የሚገባ አለመሆኑ ግልጽ ነው። እናም “ብንሄድ ይሻላል” ከሚል ሀሳብ ባንሄድ ይሻላል ለማለት ትኩረት መስጠትን ይጠይቃል።
 
በናርዶስ አዳነ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top