የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በጎፋ ዞን በደረሰው አስከፊ ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ

4 Mons Ago 740
የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በጎፋ ዞን በደረሰው አስከፊ ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ

የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት ናዳ አደጋ በደረሰው አስከፊ ጉዳት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል፡፡

የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳደር አወል አርባ የበርካታ ወገን ህይወት በቀጠፈዉ በዚህ አስከፊ አደጋ የተሰማቸዉን ጥልቅ ሃዘን በራሴና በክልሉ ህዝብ ስም እገልፃለዉ ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በደረሰው አስከፊ ጉዳት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀው፤ በዚህ አደጋ የማህበረሰባቸውን አባላት፣ ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ላጡ ወገኖች፣ እንዲሁም ለመላው የክልሉ ህዝብና መንግስት መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በምንችለው ሁሉ ከጎናችሁ የምንቆም መሆኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ ሲሉም ገልፀዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት የሰው ሕይወት በማለፉ እና ሌሎች ወገኖችም በመፈናቀላቸው የተሰማቸው ሐዘን ጥልቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በደረሰው አደጋ ማዘናቸውን ጠቁመው ከክልሉ ሕዝብና መንግሥት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሀመድ በጎፋ ዞን በድንገተኛ የመሬት ናዳ ሕይወታቸው በተቀጠፉ ወገኖች የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልጸው፤ በደረሰው እጅግ አሳዛኝ አደጋ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ጥልቅ ልባዊ ሀዘን ተሰምቶታል ብለዋል።

በአደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መፅናናትን የተመኙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሶማሌ ክልል ህዝብና መንግስት ተጎጂዎችን ለማገዝ ለሚደረገው ርብርብ ከጎናችሁ እንደሆነ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።

የሀረሪ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በተከሰተው በመሬት መንሸራተት ምክንያት በዜጎች በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፆ፤ የክልሉ መንግስትና ህዝብ በሚያስፈልገው ሁሉ ከተጎጂዎች ጎን እንደሚቆም አስታውቋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top