ከ100 ዓመታት በላይ፣ በየአራት ዓመቱ፣ ከ200 በላይ ሀገራት የተውጣጡ እጅግ አስደናቂ አትሌቶች በአንድ ሀገር ከትመው ከ300 በላይ ውድድሮች ባሉት በዘመናዊው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ይሳተፋሉ።
ታዲያ በኦሎምፒክ መድረክ ጨዋታዎቹ ብዙ አዳዲስ ክስተቶች ይስተዋላሉ። ከማይታመን የዓለም ሪከርዶች እና አሸናፊዎች እስከ አስደንጋጭ እና ደፋር የፖለቲካ ተቃውሞዎች ድረስ ታሪክ ይመዘገብባቸዋል።
እኛም ዛሬ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ አርፈን በቅርብ ርቀት ካለፉት ከዓለም ትልቁ የስፖርት ውድድር ኦሎምፒክ ስክሪኖቻችንን ያስደመሙትን የማይረሱ የመድረኩ ታሪኮችን መለስ ብለን እንቃኛለን።
*****************************************
- በ1936 የበርሊን ኦሎምፒክ ጄሴ ኦውንስ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸነፈ።
በጀርመን በናዚ አገዛዝ ውጥረት ውስጥ በነበረበት ወቅት በተካሄደው ኦሊምፒክ አሜሪካዊው የትራክ አትሌት ጄሲ ኦውንስ በ100 ሜትር፣ በ200 ሜትር፣ በ4x100 ሜትር እና በረጅም ዝላይ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘቱ አድናቆትን አስተናግዷል።
ይህም በአውሮፓውያኑ 1936ቱ ጨዋታዎች እጅግ ስኬታማ አትሌት ሲያደርገው በአንድ ኦሎምፒክ አራት የትራክ እና የሜዳ ወርቅ በማሸነፍ የመጀመሪያው አሜሪካዊ እንዲሆንም አስችሎታል። ጀርመን በ1936 ኦሎምፒክ የነጭ የበላይነትን ለማሳየት አቅዳ የነበር ቢሆንም ኦውንስ ይህንን እቅዷን በስራውና በብቃቱ አስቁሞታል።
- በ1948ቱ የለንደን ኦሎምፒክ ቪኪ ድራይቭስ በውሀ ዋና ዳይቪንግ የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ለማሸነፍ የመጀመሪያዋ እስያ-አሜሪካዊ ሆነች።
በአውሮፓውያኑ 1924 ከፊሊፒናዊ አባት እና እንግሊዛዊ እናት የተወለደችው ቪኪ ድራቭስ በብሄሯ ዙሪያ የሚደርስባትን መድልዎ እና ጭፍን ጥላቻ እየታገለች ነው ድሏን ያሳካችው። ድራቭስ በ1948ቱ የኦሎምፒክ ጨዎታዎች ከምርጥ አትሌቶች አንዷ በመሆንም ተመርጣለች።