በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተሰሩት የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች የወርቅ ምድር ላይ ተኝተን እንደነበር ያሳዩ ናቸው - የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት

1 Mon Ago 682
በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተሰሩት የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች የወርቅ ምድር ላይ ተኝተን እንደነበር ያሳዩ ናቸው - የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተሰሩት የጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ ወንጪ እና የመሳሰሉት ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች የወርቅ ምድር ላይ ተኝተን እንደነበር ያሳዩ ናቸው ሲል የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች ሰዎች የሚጠቀሙባቸው  የተለያዩ አገልግሎቶች ማግኛ ቦታዎች ሲሆኑ እንደ ሬስቶራንት የመሳሰሉ አገልግሎቶች የሚያገኙበት ነው ብለዋል፡፡

ቱሪስቱ ወደ ሀገር ሲመጣ ምንድነው ሚሰራው፣ ምን እያየ ነው የሚውለው፣ ምን ተግባር ላይ ይሳተፋል፣ ጉብኝቱ ምን ምን አገልግሎቶችን ያካታል የሚለውም ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አንስተዋል፡፡

እየተሰሩ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች ለቱሪስቱ ምቾት እና የአገልግሎት ቆይታ እንዲራዘም ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ገልፀዋል፡፡

እንደ ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ ወንጪ የመሳሰሉት ስፍራዎች ከዚህ በፊት ሪዞርት ያልነበሩና  ለጎብኚዎች ምቹ ያልነበሩ ስፍራዎች እንደነበሩም አንስተዋል፡፡

ፓርኮች፣ የተፈጥሮ ጸጋዎች ቱሪስቱ እየገባ መቆየት ሲገባው ለቆይታ ምቹ ባለመሆናችው ምክንያት ጎብኝተው በአቅራቢያው ወደ ሚገኙ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች የሚያቀኑበት አጋጣሚ እንደነበረም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመላክዋል፡፡

ጎብኚዎች ከዚህ ቀደም ማታ አምሽተው የዱር እንስሳትን ማየት አይችሉም ነበር የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጎብኚዎች ለሊት የሚወጡ እና የሚገቡ እንስሳቶችን ማየትን እየሻቱ ማየቱን አይችሉም ነበር ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሻ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የምግብ እና መጠጥ እንዲሁም የኢንተርኔት፣ መብራት አገልግሎቶች እየተሞሉ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል፡፡

የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች እንቅስቃሴ የምንላቸው ቱሪስቱ ገንዘብ እንዲያመጣ የቆይታ ጊዜው እንዲራዘም የሚፈልጉ ናቸው ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የቱሪስት መዳረሻ ሊያሟሉ የሚገባውን ብቃት እያሟሉ ይገኛሉ ሲሉም አንስተዋል፡፡

በማስጎብኘት ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እንቅፋት የነበሩባቸው ሁኔታዎች እየተቀረፉ እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እየፈረጠ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ጨበራ ጩርጩራ፣ ኮይሻ እነ ሃላላ ኬላ የተሰሩበት አካባቢ ምርጥ የሆነ የተፈጥሮ ጸጋ የተላበሰ በመሆኑ አሁን ላይ በጉዞ ጭምር ጎብኚው እንዲጎበኝ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ የተሟሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ሲገነቡ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሆኑም አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል፡፡

የቱሪስት መዳረሻዎች ሲገነቡ እንደሰንሰለት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳላቸውና  በዋናነት የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ምህዳርን እንደሚያሰፋም አንስተዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየተሰራ ባለው ስራ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ማዕከል ተማሪዎች መበራከታቸውንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡  

የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ይገኛል ብለዋል፡፡

አንድ ቱሪስት ሲመጣ ለ9 ሰው በአማካኝ የሥራ እድል ይፈጥራል የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በትራንስፖርት፣ በሆቴል በመሳሰሉ አገልግሎቶች ለዜጎች የመገበያያ መንገድን ይፈጥራሉ ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑም ሊበራከቱ ይገባል ብለዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top