አዲሱ የትብብር እና የጋራ መንገድ

10 Mons Ago 1801
አዲሱ የትብብር እና የጋራ መንገድ

እ.አ.አ በ2000 የተቋቋመው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) በቻይና እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ውይይት፣ ትብብር እና የኢኮኖሚ አጋርነት እንዲያድግ ሚያስችል የቻይና እና አፍሪካ ግንኙነት ቁልፍ መድረክ ነው።

 

ፎረሙ በቻይና እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ትስስር ያጠናክራል፡፡ ትኩረቱም እንደ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ መሰረተ ልማት፣ ትምህርት እና ጤና በመሳሰሉ ዘርፎች ትብብርን ማላቅ ነው፡፡

ፎረሙ በዘላቂ ልማት፣ በዲጂታል ሽግግር እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ላይ አተኩሮ በአፍሪካ ውስጥ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት እየሠራ ነው፡፡ ትብብሩ አፍሪካ በድህረ ኮቪድ 19 በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስተዋለ ያለውን ፈጣን ለውጥ ተቋቁማ እንድትቀጥል አስተዋጽኦ እያደረገም ይገኛል፡፡ 

በመደበኛነት በየሦስት ዓመቱ  የሚካሄድ ሲሆን፣ የፎረሙ ተሳታፊዎችም የግንኙነቱ ወሳኝ አካላት ናቸው፡፡ ከመደበኛ ጉባኤዎች በተጨማሪም የስምምነቶችን አፈጻጸም ለመገምገም ቋሚ የመከታተያ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ።

የቻይና እና የአፍሪካ ግንኙነቶችን ከፍ ያደረገው የ2006 የመጀመሪያው ጉባዔ የቻይና-አፍሪካ የልማት ፈንድ የተመሰረተበት እና በርካታ የንግድ ስምምነቶች የተደረጉበት ነበር።

 

ልዩ ውሳኔዎች ሲያስፈልግ የሀገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ስብሰባ ይካሄዳል፡፡ እ.አ.አ በ2006 ቤጂንግ፣ በ2015 በጆሃንስበርግ፣ 2018 ቤጂንግ እንዲሁም 2021 ዳካር የተካሄዱት የመሪዎች ጉባኤዎች የዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ቻይና የአፍሪካ ትልቁ የንግድ አጋር ስትሆን፣ በየዓመቱ ከአፍሪካ ጋር የምታካሂደው የንግድ ልውውጥ ከ200 ቢሊዮን ዶላር አልፏል። ፎረሙ ትኩረት የሚያደርገው የንግድ ሚዛንን ማስጠበቅ፣ በኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ለአፍሪካ ምርቶች የገበያ መዳረሻዎችን ማመቻቸት ላይ ነው።

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እየሠራች ያለችው እንደ ምዕራባውያኑ ጫናዎችን በማድረግ ሳይሆን በመላው የአፍሪካ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ነው፡፡ ከእነዚህም መሰረተ ልማቶች መካከልም መንገዶች፣ የባቡር ሐዲዶች፣ ወደቦች፣ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የተሠሩት ሥራዎች የአፍሪካን መገናኛ አውታሮችን እና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን እያሻሻሉ ይገኛሉ።

 

በሌላ በኩል ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት ብድር እና እርዳታ የምታቀርብ ሲሆን፣ እነዚህ ድጋፎችም የሚውሉት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ነው። ይህ ብድር እና ድጋፍ ብዙ የአፍሪካ ሀገራትን የሚያካትተውን የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭን ይጨምራል። 

ቻይና ሆስፒታሎችን መገንባት፣ የሕክምና ባለሙያዎችን እና የሕክምና መሳሪያዎችን ማቅረብን ጨምሮ በተለያዩ የጤና ዘርፍ ማሻሻያዎች ላይ የአፍሪካ ሀገራትን ትደግፋለች። በቻይና ሙሉ ድጋፍ በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እንዱ ማሳያ ነው፡፡

ቻይና ለአፍሪካ ተማሪዎች የነፃ ትምህርት ዕድልን በመስጠት፣ የሙያ ሥልጠና እና ክህሎት ልማት ፕሮግራሞችን በመዘርጋት ተጨባጭ ድጋፎችን እያደረገች ትገኛለች፡፡