ኢትዮጵያ የአልደፈር ባይነት፣ የነፃነት ተምሳሌት አገር ናት። ይህ ታሪክ በውጭ ወራሪ ኃይሎች ላይ ላስገኘችው ድል ትክክለኛ መገለጫ ሆኖ ቆይቷል።
በበርካታ የጦር አውድማ ውላ ያደረችው ኢትዮጵያ በአገር ውስጥም በወንድማማቾች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ብዙ ዋጋ ስትከፍል ቆይታለች።
እንዲህ ያሉ የቆዩ ታሪኮችን ለመግለጥ ቢያስፈልግ ብዙ መረጃዎች ይገኛሉ። በቅርቡም በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት አንዱ ሆኖ ይመጣል።
በርካቶች በሞት ሸለቆ ውስጥ እንዲያልፉ ያደረገው ይህ ጊዜ የብዙ ቤተሰቦችን ህይወትም ውስብስብ እንዲሆን አድርጓል።
በእርግጥ ዛሬ ዋና ትኩረቴ ስላሳለፍነው ጦርነት ማውራት አይደለም። ኢትዮጵያ አሸናፊ የሆነችበትን ስምምነት አድርጋ ይህን አስከፊ ጦርነት ካስቆመች በኋላ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያስተዋልኩትንና የሰማሁትን ማጋራት ነው የፈለኩት።
በስራ ምክንያት ከአዲስ አበባ መቐለ ከገባሁ 20 ቀናት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ቀናት መቐለን፣ ዕዳጋ ሐሙስን፣ ዓደዋን እና አክሱም ከተሞችን በጥቂቱም ቢሆን በጋዜጠኛ ዓይን ለመመልከት እድል አግኝቻለሁ።
እነዚህ ከተሞች በጦርነቱ ወቅት የመሳሪያ ድምጽ የሚሰማባቸው፣ የሰው እንቅስቃሴን የሚናፍቁ፣ አንድ አይነት ስሜት የሚስተናገድባቸው፣ ተስፋ የጨለመባቸው ዝምተኛ ከተሞች ሆነው አሳልፈዋል።
ዛሬ በከተሞቹ እንዲያ ያለው ስሜት ተገፎ ጠፍቷል፤ ይልቁንም የተስፋ ጭላጭል የሚታይባቸው የሰላም ወጋገንም የፈነጠቀባቸው ከተሞች መሆን ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
ለወትሮው ገበያ ደርሶ መመለስ ብርቅም እድልም የሆነባቸው አካባቢዎች አሁን በሰላም ወጥቶ መግባት መገበያየት መቻሉን የሰላም ዋጋው ሲኖሩበት የማይታወቅ ሲያመለጥ የሚናፍቅ ስለመሆኑ አስረጅ ምክንያት ይሆናል።
ጦርነት ጭር ያደረጋቸው የህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ማህበረሰባዊ መገናኛዎች፣ የመዝናኛ ቦታዎች እና ምግብ ቤቶች ያሳጣቸውን ሰው እና ገበያ ሰላም መልሶ አገናኝቷቸዋል።
ሰውም ተሽከርካሪም ሲናፍቁ የነበሩ የየከተሞቹ አስፋልቶች ዛሬ ላይ ያለማቋረጥ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው ሆነዋል። በእርግጥ እንዲህ ያሉ መገለጫዎችን በሰላም ጊዜ ከግምት የማይገቡ ቢሆንም ሰላም ሲጠፋ ግን እንደቀላል የማይታዩ ምን ያህል ሩቅ እንደሆኑም ለማወቅ የዛሬ 2 ዓመት እና ዛሬን መኖር ይጠይቃል።
የማያቸው ሁሉ ከፊታቸው ላይ የሚነበብ ተስፋ ይታይባቸዋል። ያገኘኋቸውም ያለፈውን አስከፊ ጊዜ እና የዛሬ ሰላምን ሲያወሩ በተመስጦ ከማዳመጥ ውጭ ምንም አያስብሉም። የሰላምን አስፈላጊነት እና የጦርነት አስከፊነት ለእኔ ለማስረዳት ትግረኛ እና አማርኛ በቀላቀሉ ድምፆች አስረድተውኛል።
የሰላም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ የጦርነት ማስታወሻዎችን አጥፍቶ የሰላም ትዕምርቶችን ለማቆም ይደረገ የነበረው ሥራ ተስፋም ስጋትም የያዘ ሆኖ ቆይቷል። በአንድ በኩል ዳግም ጦርነት ይነሳ ይሆን የሚል ፍራቻ እና ስጋት ያለባቸው ሰዎች ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በኋላ ወደኋላ ላለመለስ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በአንክሮ የሚከታተሉ ተስፈኞች ናቸው።
እዚህ ላይ አንድ ስጋት ሆኖ የሚነሳው የቀድሞ ተዎጊዎችን ወደሰላም መልሶ ከማህበረሰቡ ጋር የመቀላቀል ሂደት የዘገየ የሚመስላቸው ሰዎች እንዲጠራጠሩ ምክንያታቸው ነው። ይሁን እንጂ ከሰሞኑ እኔም ለስራ የመጣሁበት ዋናው ጉዳይ ይሄው በመሆኑ ጥርጣሬው እንዳይኖር አድርጓል።
በትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደተሃድሶ ማእከላት ለማስገባት በመጀመሪያው ዙር የነፍስ-ወከፍ እና የቡድን ጦር መሳሪያዎችን የማስረከብ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል። ይህ ሥነ ስርዓት ሲካሄድ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች በተገኙበት ጭምር ነው። ኢትዮጵያ አጋጥሟት የነበረውን ችግር በሰላም ለመፍታት የሄደችበት ርቀት ደግሞም አሁን ለሰላም ስምምነቱ ያላት ቁርጠኝነት ለታዛቢዎቹ የሚደንቅም ሆኗል።
ሜጀር ጀነራል ራዲና ስቴፈን የማስረከብ ሥነ ሥርዓቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ “ትጥቅ ማስፈታት እና ለተሃድሶ ማዘጋጅት ብዙ ጊዜ በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚከናወን ሥራ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ዓለም ከሚያውቀው የተለየ እና ብዙዎች ሊማሩበት የሚገባ ሥርዓት ነው። ይህም የሚያሳየው የራሳችሁን ስራ በራሳችሁ ለመፍታት ፍላጎቱም ሆነ አቅሙ እንዳላችሁ የሚያመላክት ነው።” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
በዓለም ላይ የሚካሄዱ ጦርነቶች በስምምነት ሲጠናቀቁ እጅግ ፈተና ሆኖ የሚመጣው እና የሰላም ሂደቱን የሚያጓትተው የትጥቅ ማስፈታት እና ወደ ማህበረሰቡ የመመለስ ሂደት በእንግሊዝኛ አጠራሩ Disarmament, demobilization, and reintegration (DDR) ነው። ለዚህም ነው በመቐለው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ብርጋዲር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ በዓለም ላይ ትልቁ የትጥቅ ማስፈታት እና ወደ ማህበረሰቡ የመመለስ ሂደት (DDR) እየተካሄደ ያለው በኢትዮጵያ ነው ማለታቸው።