ታግታ የተወሰደችው የ2 ዓመት ከ8 ወር ህፃን በተደረገ የተቀናጀ ክትትል በሦስት ቀናት ውስጥ መገኘቷን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

12 ቀን በፊት
ታግታ የተወሰደችው የ2 ዓመት ከ8 ወር ህፃን በተደረገ የተቀናጀ ክትትል በሦስት ቀናት ውስጥ መገኘቷን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

ታግታ የተወሰደችው የ2 ዓመት ከ8 ወር ህፃን የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ጋር ባደረጉት የተቀናጀ ጠንካራ ክትትል በሦስት ቀናት ውስጥ መገኘቷን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል። 

የ2 ዓመት ከ8 ወር ዕድሜ ያላት አቢጊያ ዳንኤል የተባለችው ህፃን የታገተችው በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሳርቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተወስዳ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ቸርነት ጥላሁን የተባለው ተጠርጣሪ ከቤተሰቡ ጋር በነበረው ቅርበት ሕፃን አቢጊያን በተለያዩ ቦታዎች እየወሰደ በማዝናናት እንደ ቤተሰቡ አባል ያጫውታት እንደነበረና ከአምስት ወር በላይ ከቤተሰቡ ጋር በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪነት የነበረው ቅርርብ ወንጀሉን በቀላሉ ለመፈፀም ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረለትም ነው ፖሊስ የገለፀው።

ግለሰቡ ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ/ም ከምሽቱ 12 ስዓት ተኩል ገደማ ወደ ህፃኗ ወላጆች መኖሪያ ቤት በመሄድና "እናቷ አምጣት ብላኛለች" ብሎ ለቤት ሰራተኛዋ ከነገረ በኋላ ሕፃኗን ወስዶ በማገት ገንዘብ እንዲሰጠው ከወላጆቿ ጋር ሲደራደር መቆየቱን ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪው 150ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንዲሰጠው በመጠየቅ ገንዘቡን ማግኘት ካልቻለ ሕፃኗን በህይወት እንደማያገኟት ሲዝት እንደነበረ የህፃን አቢጊያ ወላጅ እናት ለፖሊስ በሰጠችው ቃል ማስረዳቷም ነው ፖሊስ የጠቀሰው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ህፃኗን ለማስመለስና ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ቀንና ለሊት ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ በተደረገው ክትትልም ዛሬ ሚያዚያ 28 ቀን 2016 ዓ/ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አለም ሰላም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪው ተከራይቶ በሚኖርበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ለሶስት ቀናት ያህል ታግታ የቆየችው ህፃን አቢጊያ ዳንኤል  ልትገኝ መቻሏን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ህፃናት ልጆች ለእንደዚህ አይነት ወንጀል ተጋላጭ እንዳይሆኑ እንዲጠብቋቸው አደራ የተሰጣቸው ግለሰቦችም ሆኑ ሞግዚቶችና ወላጆች  ነገሮችን በጥርጣሬ በማጤንና የማረጋገጥ ሃላፊነታቸውን በመወጣት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top