የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቧል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

10 ቀን በፊት
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቧል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ አቅሞችን ወደ ስራ በማስገባት ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን አስጀምረዋል።

በንቅናቄው አማካኝነት ባለፉት 9 ወራት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉንም ገልጸዋል።

በሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተው ይህ ኤክስፖ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ 210 አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ምቹ የሆነ እምቅ አቅም እንዳላት ተናግረዋል።

ለኢንዱስትሪ ዋነኛ ግብዓት ከሆኑት መካከል ግብርና ዋነኛው መሆኑን አንስተው፣ ከዚህ አኳያ መንግስት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ የቻሉ ሰፋፊ ስራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።

በስንዴ፣ ቡና፣ ሩዝና ሻይ ምርቶች ላይ የተከናወኑ ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪ በኢነርጂና በሰው ሃይል ያሉ አቅሞችም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እነዚህ አቅሞችን ወደ ስራ በማስገባት ረገድ ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለአብነትም ባለፉት 9 ወራት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል።

በቀጣይ በግብርና ምርታማነት ላይ የተመዘገበውን ስኬት መሸከም የሚችል የኢንዱስትሪ ልማት መገንባት ይገባል ነው ያሉት።

የአገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህልን ማዳበር እንደሚገባም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄው ሚያዚያ 2014 ዓም የተጀመረ ሲሆን እስከ 2024 ዓም ተግባራዊ ይደረጋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top