የ9 ወር አፈፃፀም ሪፖርቱ ከ75 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆናችንን ያሳያል፡- የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን

10 Days Ago 190
የ9 ወር አፈፃፀም ሪፖርቱ ከ75 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆናችንን ያሳያል፡- የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን

የሀገሪቱን ቁልፍ ችግሮች ለመፍታት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፤ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ የጋራ ማንነት ለመገንባት እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግስት እንዲኖርም አዲንዲሁ፡፡ “አካታችነት” የሚለውን ሃሳብ መርሁ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ፡፡

ኢትዮጵያ የገጠማት የታሪክ ስብራት በኃይል ሳይሆን በንግግር እና በመወያየት መጠገን አለበት በሚል ኢትዮጵያ እየመከረች ነው፡፡

በውጤቱም የሚታዩ ችግሮች ተፈተው እንደ ሀገር በአንድነት እና በመቻቻል ላይ የተመሰረቱ  ልዩነቶችን አምኖ መቀበል ይጠበቃል፡፡

ሆኖም ግን ይህን በማድረግ ሂደት ውስጥ በሀገሪቱ  ያለው ያለመረጋጋት አንዱ ተግዳሮት እንደሆነ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ይገልፃሉ፡፡

ኮሚሽኑ አሁን ላይ ከአማራ እና ከትግራይ ክልል በስተቀር ለመጨረሻው ምዕራፍ  ቅድመ ዝግጅት ላይ እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡

በዚህም  እስካሁን የተለዩት፤ ተሳታፊዎችን የሚያወያዩ አጀንዳ ልየታ ላይ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጥበቡ ኮሚሽኑ በምክክሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑትን ለይቶ ማጠናቀቅ  እንደ ግብ የያዘው ቢሆንም፤ያሉ አለመረጋጋቶች ተፈፃሚነቱን እያጓተቱ ነው ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ገለልተኝነትን የተላበሰ መሆኑን አስታውሰው፤ ለምናነሳው ጥያቄ መንግስት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል እያደረገው ያለው እገዛ እና ድጋፍ የሚበረታታ ነው ሲሉ ያነሳሉ፡፡

እስከ ዛሬ በመጣነው መንገድ ሀገራዊ ምክክርን አጀንዳ ማድረግ ፣ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በምክክር ዙሪያ እንዲሰባሰቡ ማስቻል  እና ችግሮችን በንግግር መፍታት የሚለውን እሳቤ በማህበረሰቡ ዘንድ ማስረፅ መቻሉ እንደ አንድ ግብ እንደሚቆጥርም ነው  አቶ ጥበቡ የተናገሩት፡፡

ለ3 ዓመት ተይዞ በነበረው ዕቅድ መሰረት በፌዴራል፣ በክልል እንዲሁም ከሀገር ውጪ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ "አካታችነት" የሚለውን መርሃችንን ከሁለቱ ክልሎች ውጪ ተግባራዊ ማድረግ ችለናልም ብለዋል፡፡

በዚህም በ2016 በጀት ዓመት የ9ወር አፈፃፀም ሪፖርት ከ75 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆናችንን ያሳያልም ነው ያሉት፡፡

አቶ ጥበቡ እንደሚሉት፤ ኮሚሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ እንደተመለከተው ማህበረሰቡ በፊት ብሎም አሁን ላይ እየተጋፈጠው ካለው ችግር በመውጣት ሰላም እንዲሰፍን፣ድህነት እንዳይባባስ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት ይፈልጋል፡፡

በዚህም በቀጣይ የኮሚሽኑ እንቅስቃሴዎች መሰረታዊ እና ሀገራዊ የሚመስሉ ችግሮች የትኞቹ ናቸው፤ ምንጫቸውስ ምንድነው የሚሉ ሃሳቦች  የሚታዩ ይሆናል ብለዋል፡፡

ምክክር ትልቅ እንደመሆኑ ሁላችንም ቁጭ ብለን መነጋጋር ያስፈልገናል የሚሉት የዓለም የሰላም እና የመልካም ስነ-ምግባር አምባሳደር የሆኑት አቶ ታደለ ደርሰ ግርማ  ናቸው፡፡

አቶ ታደለ እስከ ዛሬ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ይነጋገራል፤ ነገር ግን መደማመጥ ስለሌለ እና የሀሳብ ልዩነቶችን ማቻቻል ባለመቻሉ ዛሬ ላለንበት ደረጃ ደርሰናል ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የጀመረው ተግባር ጥሩ ሆኖ በተቀመጠለት ጊዜ ኃፊነቱን አለመወጣቱን  ያነሳሉ፡፡ ያሉብን ችግሮች የኮሚሽኑን ተግባር እየቀደሙት እንዳይሄዱም ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡

ለኮሚሽኑ ተግበራ እንቅፋት አንዳይሆኑም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች አፋጣኝ ንግግርን የሚሹ መሆናቸውን አቶ ታደለ አንስተዋል፡፡     

ኮሚሽኑ የሚገጥሙት ተግዳሮቶች አይኖሩም ማለት ባይቻልም፤ እነርሱን ለመፍታት ከመደበኛ እውቀት ባሻገር ሀገር በቀል የሆኑ መንገዶችን መመልከት ይገባልም ነው የሚሉት፡፡

ለዚህም የኃይማኖት ተቋማትን ፣የሲቪክ ማህበራትን፣ባለድርሻ አካላትን ማካተት አስፈላጊ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡

በአሶሳ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ ዜናው ዓለም በበኩላቸው፤ ሀገራት ባለመግባባት እና በግጭት ውስጥ ሲያልፉ ከችግር አሻግሮ ለማየት ምክክር ይጠቅማል ሲሉ ይገልፃሉ፡፡

በምክክር ኮሚሽኑ ከምሁራን አንስቶ ብዙኀኑን ለማካተት የተደረገው ሂደት የሚበረታታ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡

ይህን መነሻ በማድረግ የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ግዜ እንድትመክር የሄደበት መንገድ መልካም የሚባል መሆኑን ነው የገለፁት፡፡

ኮሚሽኑ የተለያዩ ተግዳሮቶችን በማለፍ የአጀንዳ እና የተሳታፊ ልየታ ላይ መድረሱ ትልቅ ውጤት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

 በአፎሚያ ክበበው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top