ዘላቂ ደህንነታችን ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ፈጠራ እና ኅብረትን ይፈልጋል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

1 Yr Ago
ዘላቂ ደህንነታችን ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ፈጠራ እና ኅብረትን ይፈልጋል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ "የእኛ እና የመጪው ትውልድ ደህንነት እንዲረጋገጥ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ፈጠራ እና ኅብረታችን ያስፈልጋል" ሲሉ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን የተናገሩት በአቡ ዳቢ ዓለም አቀፍ ‘ሰስቴኔቢሊቲ' ሳምንት ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
በዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሚመክረው ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አጋርተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት በግሉ ዘርፍ የሚመራ፣ ተወዳዳሪ፣ በሀብት የተጠናከረ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚን በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስቀጠል ያለመ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ አውጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና አይሲቲ ለመሳሰሉ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች ቅድሚያ የሰጠው የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም፣ በዘላቂ ዕድገት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አካታች የብልጽግና አጀንዳ ለዜጎች ምቹ ኑሮን መፍጠር፣ ፅናትን በመገንባት እና ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ መሠረትን መጣል ላይ የተመሠረተ እንደሆነም ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ ታዳጊ ሀገራት አንዷ መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “ይህንን የተጋላጭነት ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በሀገራችን በሁሉም ዘርፎች የአየር ንብረት ለውጥን የመላመድ አስፈላጊነትን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብተናል” ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ መንደፏን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ባለፉት አራት ዓመታት 25 ሚሊየን ዜጎችን በማሳተፍ 25 ቢሊዮን ችግኞች መትከል መቻሏንም ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top