ህይዎት የእሱን ያክል የፈተነችው ያለ አይመስልም። ከታላላቆቹ የአውሮፓ ሊጎች አንዱ በሆነው ጣልያን ሴሪ ኤ ለመጫዎት ያለፈበት መንገድ እጅግ ፈታኝ ነው። በሚላን ቪዞሎ የተወለደው ፍራንቺስኮ አቼርቢ በሀገሪቱ 2ኛው የሊግ እርከን ለብዙ ክለቦች ተጫውቷል።
በተለይ በ2010/11 በሴሪ ቢ ይሳተፍ የነበረውን ሬጊናን ወደ ሴሪ ኤ ለመመለስ የከፈለው ዋጋ እና በመከላካሉ ያሳየው ድንቅ ብቃት የትልልቅ ክለቦች አይን ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
ከዚህ በኋላ በቼቮ ቬሮና፣ ጀኖዋ፣ እና ኤሲ ሚላን ቢየሳልፍም በሚፈልገው ልክ የመጫዎት ዕድል አላገኝም።
አቼርቢ 2013 ላይ ወደ ሴሪ ኤ ያደገውን ሳሱሎን በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዩሮ ተቀላለቀ። ተከላከዩ ለሊጉ አዲስ ወደ ሆነው ክለብ ካመራ በኋላ አንድም ጨዋታ ሳያደርግ በሰውነቱ ውስጥ የካንሰር ምልክት እንደሚያሳይ በዶክተሮች ተነገረው።
በሚላን የተሳካ ህክምና አድርጎ ዳግም ወደ ጨዋታ ተመለሰ። ከህክምናው በኋላ ለአዲሱ ክለቡ ድንቅ ብቃቱን ቢያሳይም በህይወቱ ፈተና የማያጣው አቼርቢ ከ13 ጨዋታዎች በላይ ማድረግ አልቻለም።
በሳሱሎ እያለ በተደረገለት ምርመራ ሳያውቅ በተጠቀመው መድሀኒት ለስፖርተኞች የተከለከለ እና በህገወጥ መንገድ ጥቅም ላይ የዋለውን ቴስቲስትሮን የሚጨምር (gonadotropin) የተባለ አበረታች ንጥረ ነገር በሰውነቱ ውስጥ በመገኝቱ በጣልያን እግር ኳስ ፌደሬሽን እገዳ ተጣለበት።
የእግር ኳስ ህይወቱ አደጋ ላይ የወደቀው ፍራንሲስኮ አቼርቢ እገዳ ላይ እያለ በተሰማው የህመም ስሜት ወደ ሆስፒታል ሲያመራ ቀድሞ የታየበት የካንሰር ህመም ወደ ሌላ ደረጃ ተሸጋግሮ የዘር ከርጢት ካንሰር እንዳለበት ተረጋገጠ።
የካንሰር ደረጃው አይደለም ዳግም ብዙ ወደ ሆነለት እግር ኳስ መመለሱ ይቅርና በህይወት የመቆየቱን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ከተተው። በርካታ የጣልያን ጋዜጦችም የአቼርቢ የእግር ኳስ ህይወት በሚያሳዝን ሁኔታ ተጠናቀቀ በማለት ዘገባዎች ሰሩ፡፡
ለነገሮች በፍጹም እጅ መስጠት የማያውቀው ጣልያናዊው ተከላካይ ለ6 ወራት የእግር ኳስ ልምምዱን ከህክምናው ጋር በሚገባ ሲከታተል ቆይቶ 2014 መጋት 15 ቀን አሁን ሁሉም ነገር ተጠናቋል ለጨዋታ ዝግጁ ነኝ በማለት በፌስቡክ ገጹ አስነበበ፡፡
እነዚያ ሞቱን ሲጠብቁ የነበሩ ጋዜጦች ስለ አስገራሚው ሰው ታሪክ መጻፍ ጀመሩ። እሱም ለህይወቱ አደጋ የሆነውን ካንሰር አሸንፎ ለሳሱሎ በአጠቃላይ 157 ጨዋታችን አደረገ፡፡
2018 ላይ ወደ ላዚዮ ያመራው አቼርቢ በሴሪ ኤ ታሪክ በ149 ተከታታይ ጨዋታች ላይ በመሰለፍ 162 ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ከቻለው ሀቪየር ዛኔቲን በመቀጠል ሌላ ታሪክም ሰርቷል፡፡
በ2022 ከላዚዮ ወደ ኢንተር ሚላን የተዛወርው ፍራንሲስኮ አቼርቢ ትላንት ምሽት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሌላ ተአምር የሰራበትን ምሽት አሳልፏል።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ኢንተር ሚላን ባርሴሎናን አሸንፎ ለፍጻሜ እንዲደርስ ትልቁን ሚና ተወጥቷል።
በጁሴፔ ሜዛ በተደረገው ጨዋታ እስከ 90ኛው ደቂቃ 3 ለ 2 ሲመራ የነበረው ኢንተር ሚላን በ3 አመት ውስጥ ለ2ኛ ጊዜ ለፍጻሜ ለመድረስ ያለው ተስፋ ቢያበቃም የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ በባከነ ደቂቃ ከካንሰር ያመለጠው ሰው የኢንተርን 3ኛ ግብ ከመረብ አሳረፈ።
በአቼርቢ ግብ ወደ ጨዋታ የተመለሰው ኢንተር በተጨመረው 30 ደቂቃ አንድ ግብ አስቆጥሮ ከ15 አመት በኋላ በአውሮፓ መድረክ ለመንገስ ለፍጻሜ የደረሰበትን ውጤት አስመዘገበ።
አውሮፓ ላይ ካሉ እንደ ሃላንድ፣ ሃሪ ኬን እና ሮሜሉ ሉካኩ አይነት ታላላቅ አጥቂዎች ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን ያሸነፈው ፍራንቺስኮ አቼርቤ በምሽቱ ፍልሚያ የባርሴሎናን አስፈሪ አጥቂ ተቋቁሞ ከሚጠበቅበት መከላከል በላይ አጥቂ ሆኖ ተአምር የሰራበትን ምሽት አሳልፏል።
በአንተነህ ሲሳይ