በኢትዮጵያ የከተሞች ብዛት ከ2 ሺህ 500 አለፈ

1 Yr Ago
በኢትዮጵያ የከተሞች ብዛት ከ2 ሺህ 500 አለፈ
በኢትዮጵያ ያሉ የከተሞች ብዛት ከ2 ሺህ 500 ማለፉን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ትግበራ ሰነዶች ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ በኢትዮጵያ ፈጣን የሆነ የከተሜነት ምጣኔ መኖሩን እና አሁን ላይ በሀገሪቱ ያሉ ከተሞች ብዛት ከ2 ሺህ 500 በላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“በኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ዕድገቱ (ጂዲፒ) ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን እያመነጩ ይገኛሉ” ሲሉም ገልጸዋል።
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከግብርና በመቀጠል ለዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል እየተፈጠረበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይሁንና የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከአቅም ውስንነት የሚመነጭ የተወዳዳሪነት ክፍተት እንዳለበት ጠቅሰዋል።
በማዕቀፍ ተይዘው እየተተገበሩ ያሉ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቶች ይህንን በመቅረፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ በበኩላቸው፣ ለዘርፉ አለማደግ የአቅም ክፍተት እንቅፋት መሆኑን እና ኢንስቲትዩቱ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የውይይቱ አላማ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች የአቅም ክፍተት መለየት እና የድጋፍ ሥርዓት ትግበራ ላይ ያተኮረ መሆኑም ተገልጿል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top