በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በጎንደር ከተማ የተገነባው የዳቦና የዱቄት ፋብሪካ ተመርቆ ስራ ጀመረ

1 Yr Ago
በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በጎንደር ከተማ የተገነባው የዳቦና የዱቄት ፋብሪካ ተመርቆ ስራ ጀመረ
በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በጎንደር ከተማ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የዳቦና የዱቄት ፋብሪካ ዛሬ ተመርቆ ስራ ጀመረ።
ፋብሪካውን መርቀው የከፈቱት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው።
ፋብሪካው በቀን 400 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፤ ለጎንደር ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ ማቅረብ የሚያስችል ነው።
ፋብሪካው 160 ለሚሆኑ ስራ አጥ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ተናግረዋል።
ፋብሪካው በዘመናዊ የዳቦ ማምረቻ ማሽኖች የተደራጀ ከመሆኑም በላይ የዳቦ ማመላለሻ ተሽከርካሪ የተመደበለት መሆኑንም ገልጸዋል።
በከተማው አማካኝ ቦታዎች በተቋቋሙ የዳቦ መሸጫ ሱቆች አማካኝነት የዳቦ ስርጭት በየዕለቱ ለከተማው ነዋሪዎች ተደራሽ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ለፋብሪካው ግንባታ የከተማ አስተዳደሩ 11 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ በነጻ የሰጠ ሲሆን፤ ግንባታውንም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉ ተገልጿል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ የአማራ ክልልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ነዋሪዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top