በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅራቢ ተቋማት ደንበኞችን ይቅርታ ጠየቁ

1 Yr Ago
በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ እና የውሃ አቅራቢ ተቋማት ደንበኞችን ይቅርታ ጠየቁ

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን በመዲናዋ ሰሞኑን በተከሰተው የኤሌክትሪክ እና ውሃ መቆራረጥ ደንበኞችን ይቅርታ ጠየቁ።

ሁለቱ ተቋማት ባለፋት ሁለት ሳምንታት በከተማዋ በተስተዋለው የውሃ እና ኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ዙሪያ በከንቲባ ጽ/ቤት የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሰሞኑን በመዲናዋ የተከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ገበየው ልካሳ ተናግረዋል።

ከዝናቡ በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ስራዎች ግንባታና በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ የሚፈፀም ስርቆትና መሰል ድርጊቶች ለኃይል መቆራረጡ ምክንያት መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ፣ የውሃ አቅርቦት ለመቆራረጡ በከተማው ያለው የውሃ ፍላጎትና አቅርቦት ያለመጣጣም፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እና መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ምክንያት ነው ያሉት የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቃዱ ዘለቀ ናቸው።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአጭርና የረጅም ጊዜ ፕሮጀክቶች መቀረጻቸው ተገልጿል።

ሁለቱ ተቋማት ሰሞኑን በተከሰተው የኤሌክትሪክ እና  ውሃ መቆራረጥ ደንበኞችን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

በፍሬህይወት ረታ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top