በእስራኤል ላይ የማትጨክነው አሜሪካ የገባችበት አጣብቂኝ

1 Mon Ago
በእስራኤል ላይ የማትጨክነው አሜሪካ የገባችበት አጣብቂኝ

ጋዜጠኛ እና የፍልስጤም ዜና መዋዕል አዘጋጅ እንዲሁም በዓለም አቀፍ እስልምና ጉዳዮች ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆነው ራምዚ ብራውድ "የባይደን አስተዳደር ውሳኔ ወደ ቋሚ ፖሊሲ ይለወጣል ብሎ መጠበቅ ዋሽንግተን ላይ ያለውን የእስራኤልን ጠንካራ እጅ መዘንጋት ነው" ይላል፡፡

መጋቢት 25 ቀን 2024 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፀጥታው ምክር ቤት "ለረመዳን ጾም አፋጣኝ ተኩስ አቁም" በሚል የቀረበውን 2728(2024) የውሳኔ ሀሳብን አሜሪካ በድምጸ ተዐቅቦ ማለፏ ያልተጠበቀ ውሳኔ ነበር፡፡

ቀኝ አክራሪ የሚባለው የቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥትም "ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ሃማስ ተጨማሪ የማገገሚያ ጊዜ እንዲያገኝ ያደርጋል በሚል ተችቶታል” ይህም የታገቱ እስራኤላውያን እንዳይለቀቁ በር ይከፍታል የሚል ስጋትም ጭምር ነበረው። ተኩስ አቁም ከታወጀ ሃማስ ታጋቾቹን ሳይለቅ የመደራደሪያ ጊዜ ያገኛል ባይ ነው የኔታኒያሁ መንግሥት፡፡

ከአሜሪካ ውሳኔ በኋላ የእስራኤል ራፋን መያዝን አስመልክቶ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ለማድረግ አቅዳ የነበረችው እስራኤል ይህን ሃሳቤን ሰረዤዋለሁ በማለት በአሜሪካ ውሳኔ የተሰማትን ቅራኔ ገልጻለች።

ለመሆኑ ጉዳዩ እንዴት እዚህ ደረሰ? እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ዘመቻ "ራስን በመከላከል" ሽፋን ስትደግፍ የነበረችው አሜረካ በመጨረሻ እንዴት አቋሟን ልታላላ ቻለች?

ለነዚህ ጉዳዮች ምላሽ ለማግኘት ወደኋላ መለስ ማለትን ይጠይቃል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሥልጣን ጊዜያቸው ሊጠናቀቅ ሦስት ሳምንት ሲቀረው "ፍልስጤማውያን በምድራቸው ነጻ ህዝብ የመሆን መብት አላቸው" የሚለውን ሀሳብ በመደገፋቸው መነጋገሪያ መሆናቸው አይዘነጋም። በአንጻሩ ደግሞ ለእስራኤል ከፍተኛ የመከላከያ ድጋፍ በመስጠት በአሜሪካ ታሪክ ብቸኛው መሪም ናቸው፡፡

 

በአውሮፓውያኑ ታኅሳስ 23 ቀን 2016 በኦባማ የመጨረሻ የሥልጣን ዘመን የፀጥታው ምክር ቤት፣ "የእስራኤል የፍልስጤም ሰፈሮችን በኃይል መያዝ ተቀባይነት የላቸውም፤ ድርጊቱም በግልጽ ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሰ ነው" የሚለውን 2334 (2016) የውሳኔ ሀሳብ አሜሪካ በድምጸ ተዐቅቦ አልፈዋለች፡፡

ይህን ውሳኔም ለአሜሪካ አዛዥ ትሁን ታዛዥ የማታስታውቀው እስራኤል "አሳፋሪ እና ድብቅ ዓላማ ያለው" በማለት ገልጸዋለች። እዚህ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በተለያየ ጊዜ ስልጣን የሚቀያየሩ ጥሩ ጎረቤታሞች የይምሰል ድራማ የመስራት ልምዳቸው አይዘነጋም።

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሥልጣን ዘመናቸው ለእስራኤል ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የመከላከያ በጀት ድጋፍ በተጨማሪ የሚሳኤል መከላከያ ማበልፀጊያ 500 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል። ይህን ሁሉ በማድረግ ጊዜያቸውን የተጠቀሙት ፕሬዚዳንቱ በእስራኤል ዘንድ ግን "በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ከሁሉ የከፋው ፕሬዚዳንት" የሚል ተቅጽላ ስም ከማሰጠት አላተረፋቸውም።

ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ኦባማ እና ዴሞክራቶች ሠሩ ያሉትን "ክህደት" አሜሪካ ዳግመኛ እንደማትሠራ ለማስታወስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩትን ኒኪ ሄይሊን ወደ ቴልአቪቭ እስከ መላክ ደርሰው ነበር፡፡

እንደውም እኚሁ አወዛጋቢ ፕሬዚዳንት "አሜሪካ በዓለም ላይ ከእስራኤል የበለጠ ወዳጅ የላትም" ከሚለው ንግግራቸው እልፍ ብለው "ሹል ተረከዝ ያለው ጫማ እጫማለሁ፤ ይህን የማደርገው ለፋሽን መግለጫ ሳይሆን አንድ ወዳጃችን እስራኤልን የሚመለከት ችግር ካየሁ ልረግጥበት ነው" በማለት ለእስራኤል ያላቸውን ፍጹም ታማኝነት እስከ መናገር ደርሰው ነበር።

የእስራኤልን ጉዳይ ለዴሞክራቶች መምቻ ልምጭ አድርገው የሚጠቀሙት ሪፐብሊካኖች ታዲያ ቃላቸውን ለመፈጸም ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ በ2018 ፕሬዚዳንቱ ኤምባሲያቸውን ከቴላቪቭ ወደ እየሩሳሌም በማዛወር በእስራኤል እና አጠቃላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያላቸውን የውጭ ፖሊሲ አቅጣጫ ግልጽ አድርገዋል፡፡

የአሁኑ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ሲመጡም የትራምፕ ከእስራኤል አንጻር የተከተሉትን ፖሊሲዎች በማፍረስ ላይ አልተጠመዱም፡፡ ይልቁንስ “የአሜሪካ መንግሥት በዌስት ባንክ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ እና መረጋጋትን ለመጠበቅ ባለሙያ እና ተጠያቂ የፀጥታ እና የወንጀል ፍትሕ ተቋማትን ለመገንባት እንፈልጋለን" በማለት ነው ጉዳዩን ሚዛናዊ ለማድረግ ጥረት ያደረጉት፡፡

በዚህ ውሉ ባልለየው አቋማቸው ምክንያትም በተለይ በእስራኤል እና ሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አንቶኒ ብሊንከን ብዙ ቢወጡ ቢወርዱም ስንዝር ፈቀቅ ሳይል እዚህ ደርሷል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እስራኤልን ብቻ የወገነ የውጭ ፖሊሲን ማራመድ ለሪፐብሊካኖችም ጭምር ቀላል እንዳልሆነ በአሜሪካ ወጣቶች እና በዴሞክራት ፓርቲ ደጋፊዎች ዘንድ እያደገ የመጣው የፍልስጤማውያን ድጋፍ ማሳያ እየሆነ ይመስላል፡፡

"ጋለፕ" የተሰኘ ተቋም ባሰባሰበው የህዝብ አስተያየት ባለፉት አሥር ዓመታት 49 በመቶ አሜሪካውያን ለፍልጤማውያን ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ ሲሆን፣ 38 በመቶ ደግሞ አሉታዊ ነው ብሏል፡፡

በኩዊኒፒያክ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ጥናት ደግሞ ከ35 ዓመት በታች የሆኑ ዴሞክራቶች እና የዴሞክራቶችን ሃሳብ የሚያራምዱ አሜሪካውያን የባይደንን ለእስራኤል ያደላ አቋም ይቃወማሉ፡፡

የአሶሼትድ ፕሬስ የሕዝብ ጉዳይ ምርምር ማዕከል ያካሄደው ጥናትም 62 በመቶ የሚሆኑት ዴሞክራቶች ወታደራዊ እርምጃው ገደቡን እንዳለፈ የሚያምኑ ናቸው ብሏል።

ይህ በአዲሱ የአሜሪካ ትውልድ መካከል እያደገ የመጣው ለፍልስጤማውያን የማድላት ሁኔታ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እና ፖለቲከኞችን ዋጋ እያስከፈለ እንደሚገኝም ከሌሎች ጥናቶች ጋር ተዳምሮ አመላካች መሆኑ ይነሳል።

በታሪክ ሲታይ፣ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጥቅሞቿን፣ የእስራኤል ደም ያላቸው አሜሪካውያንን እና የእስራኤል ደህንነት ላይ የተመሰረተ ነበር።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ሃማስ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሱን ተከትሎ እስራኤል እየወሰደችው ያለው ወታደራዊ ዘመቻ የአሜሪካ እና እስራኤል ጉዳይ ዳግም አጣብቂኝ ውስጥ የገባ አስመስሎታል።

የካቲት 27 ቀን 2024 የተሰበሰበ የአሜሪካ የሕዝብ አስተያየት ውጤት እንዳመለከተው ሁለት ሦስተኛ (67 በመቶ) የሚሆኑት አሜሪካውያን በጋዛ ያለው ጦርነት እንዲቆም ይፈልጋሉ።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን የተሳተፉበት እና በተለያዩ ግዛቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች የተካሄዱ ተቃውሞዎችም ሌላው አሜሪካን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተታት የሚመስሉ ገጽታዎች እየሆኑ ነው።

እናም እንዲህ ያለው ከውስጥም ከውጭም እየበረታ ያለው ጫና አሜሪካ በፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ምንም እንኳ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ቢኖራትም ድምጸ ተዐቅቦ እንድትመርጥ ሳያስገድዷት እንዳልቀሩ ነው የሚነሳው።

እንጂ ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሜሪካ ከእስራኤል ጋር ያላትን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመሰረታዊነት ለመቀየር ሃሳቡም ሆነ ፍላጉቱ የላትም።

ለዚህም ነው በአሜሪካ ውስጥ ያለውን ጠንካራ የእስራኤል መሰረት ዘንግቶ የባይደን አስተዳደር ውሳኔ ወደ ቋሚ የፖሊሲ ለውጥ ይመጣ ይሆን እንዴ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው የሚባለው።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top